Fana: At a Speed of Life!

የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ፈቃድ መስጠት የሚያስችል መመሪያ ወደ ትግበራ ገባ

 

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ፈቃድ መስጠት የሚያስችል መመሪያ በካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ወደ ትግበራ እንዲገባ ተደረገ፡፡

ባለሥልጣኑ ለሰነደ ሙዓለ ንዋዮች፣ ለተዛማጅ ውሎችና ለያልተማከለ የጠረጴዛ ዙሪያ ገበያዎች ፈቃድ የሚሰጥበትና የሚቆጣጠርበትን “የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች፣ የተዛማጅ ውሎች እና ያልተማከለ የጠረጴዛ ዙሪያ ገበያዎች የፈቃድ አሰጣጥ፣ የአሰራር እና የቁጥጥር መመሪያ” አዘጋጅቶ በፍትህ ሚኒስቴር ማስመዝገቡ ተመላክቷል፡፡

በመሆኑም “የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች፣ የተዛማጅ ውሎችና ያልተማከለ የጠረጴዛ ዙሪያ ገበያዎች የፈቃድ አሰጣጥ፣ የአሰራር እና የቁጥጥር መመሪያ ቁጥር 1009/2016 ከዛሬ ጀምሮ ስራ ላይ ውሏል።

መመሪያው የሰነደ ሙዓለንዋዮች፣ የተዛማጅ ውሎች እና ያልተማለከ የጠረጴዛ ዙሪያ ገበያ ፈቃድ ለማውጣት መሟላት ስለሚገባቸው መስፈርቶች፣ ገበያው አባላቱን እንዴት እንደሚቆጣጠር፣ገበያው አባላቱን መቆጣጠር የሚያስችለው የውስጥ ደንብ በባለሥልጣኑ አጸድቆ ማውጣትእንደሚገባው፣ ለባለሥልጣኑ ሪፖርት እንዴት እንደሚያቀርብና በአጠቃላይ አሰራሩ ምን መምሰል እንዳለበት የተለያዩ ደረጃዎችን ያስቀምጣል፡፡

ይህ መመሪያ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰነደ መዓለ ንዋዮች ገበያንና ያልተማከለ የጠረጴዛ ዙሪያ ገበያን ፈቃድ ለመስጠት የሚያስችል ሲሆን÷ የመንግስትና የግል ድርጅቶች ገበያውን በመጠቀም የድርጅቶችን የድርሻ እና የብድር ሰነዶችን በመሸጥ እና ገንዘብ በመስብሰብ ፕሮጀክቶችን ለመስራት አቅም ለመፍጠር ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል መመሪያው የድርሻ ወይም የብድር ሰነድ መግዛት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ወይም ባለሃብት ፈቃድ ካለው ገበያ አስፈላጊው ቁጥጥርና ግልጸኝነትበተሟላበት የግብይት አሰራር፣ ፈቃድ ባለው ተገበያይ አማካኝነት የተፈቀዱ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮችን ለመግዛት እና ለመሸጥ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም ተገልጿል፡፡

ይህም በተበታተነ መልኩ የሚደረገውን የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ግብይት ወደ አንድ ፈቃድ ወደሚሰጠው እና ቁጥጥር ወደሚደረግበት ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በማምጣት ዘርፉ ለተዋናዮቹ እና ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተው አስተዋጽዖ የጎላም ነው የተባለው፡፡

መመሪያው በመቋቋም ላይ ለሚገኘው የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ አክሲዮን ማህበር በመመሪያው መሠረት አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታዎች ሲያሟላ ፈቃድ በመስጠት ሥራ ለማስጀመር የሚያስችል መሆኑም ተመላክቷል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.