ኢትዮጵያና ግሪክ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር ተስማሙ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከግሪክ ውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር አሌክሳንድራ ፓፓዶፖሎ ጋር በአቴንስ ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም÷ አምባሳደር ምስጋኑ መንግስት ሀገራዊ ሰላምን ለማረጋገጥ የወሰዳቸውን አዎንታዊ እርምጃዎች አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በተለይም በፕሪቶሪያው ስምምነት አተገባበር፣ በታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር፣ በብሔራዊ ሁሉን አቀፍ የምክክር መድረክ እና በብሔራዊ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አተገባበር ዙሪያ ገለጻ አድርገዋል፡፡
ኢትዮጵያና ግሪክ ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላቸው የጠቆሙት አምባሳደር ምስጋኑ÷ሀገራቱ ግንኙነታቸውን በኢኮኖሚያዊና ፓለቲካዊ መስኮች የበለጠ ማሳደግ እንዳለባቸው አንስተዋል።
በተለይም በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በትምህርትና ስልጠና ዘርፎች ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር በትኩረት መስራት አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
አሌክሳንድራ ፓፓዶፖሎ በበኩላቸው ÷ግሪክና ኢትዮጵያ ረጅም ዘመናት ያስቆጠረውን ግንኙነታቸውን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ተጨባጭ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ትብብሮችን ሊያሰፉ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ግሪክ በታዳሽ ኢነርጂ ልማት ዘርፍ ያላትን ተሞክሮ አንስተው በአየር ንብረት ለውጥ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመስራት ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል።
ሁለቱ ወገኖች ኢኮኖሚያዊ ግንኙነታቸውን ለማጠናከርና ትኩረት በሚሹ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች በጋራ ለመስራት እንዲሁም በባለብዙ ወገን መድረኮች ትብብራቸውን ለማጠናከር መስማማታቸውንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡