ከሰሞኑ ያጋጠመው የአይቲ እክል በ8 ነጥብ 5 ሚሊየን ኮምፒውተሮች ላይ ጉዳት አድርሷል ተባለ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከሰሞኑ ያጋጠመው የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን (አይቲ) እክል 8 ነጥብ 5 ሚሊየን ያህል ኮምፒውተሮች ላይ ጉዳት ማስከተሉን ማይክሮሶፍት አስታወቀ።
ክራውድስትራይክ ከተሰኘ የሳይበር ደህንነት ኩባንያ ለደንበኞቹ ባሰራጨው ሶፍትዌር ጋር በተያያዘ በተፈጠረ የአይቲ መደነቃቀፍ በርካታ ተቋማት አገልግሎት አሰጣጣቸው ላይ የከፋ አሉታዊ ጫና ፈጥሮ መቆየቱ ይታወቃል።
ችግሩ የዲጂታል አገልግሎት ለመስጠት እንዳይቻል ከማድረጉም በላይ በንብረት ላይ ጉዳት ማስከተሉን የገለጸው ማይክሮሶፍት፤ 8 ነጥብ 5 ሚሊየን ያህል ኮምፒውተሮች ከጥቅም ውጪ መሆናቸውን ገልጿል።
በኮምፒውተሮቹ ላይ የደረሰው ጉዳት በታሪክ አስከፊው የሳይበር ጉዳት መሆኑ ተመላክቷል።
ከዚህ ቀደም በፈረንጆቹ 2017 ከሳይበር ጥቃት ጋር በተያያዘ በ150 ሀገራት በሚገኙ 300 ሺህ ኮምፒውተሮች ላይ የደረሰው ጉዳት በአስከፊነቱ እንደሚታወስ ተጠቅሷል።
ማይክሮሶፍት ለጉዳት የተዳረጉ ኮምፒውተሮችን መልሶ ለአገልግሎት ለማብቃት ጥረት እያደረገ ማስታወቁን ቢቢሲ ዘግቧል።
ባጋጠመው የአይቲ ችግር አማካኝነት ለጉዳት የተዳረጉ ኮምፒውተሮች ቁጥር ከዚህም በላይ ሊያሻቅብ እንደሚችልም ተነግሯል።
በአይቲ እክሉ የተነሳ በርካታ ተቋማት አገልግሎት መስጠት አቋርጠው እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፤ በአየር መንገዶች፣ በባንኮች፣ በሚዲያዎች እንዲሁም በጤና ተቋማት ላይ ያስከተለው ጫና ከባድ እንደነበር ዘገባው አንስቷል።