የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለያዩ ሀገራዊና የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ እየመከሩ ነው
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች በተለያዩ ሀገራዊና በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ እየመከሩ ነው።
በመድረኩ ላይ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አደም ፋራህ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ደስታ ዲንቃን ጨምሮ ሌሎች አመራሮችና የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ተገኝተዋል።
አቶ አደም ፋራህ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የውይይት መድረኩ የቀጠለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በነበራቸው ውይይት ቀጣይ ውይይቶች እንደሚደረጉ በገለጹት መሰረት ነው ብለዋል።
በመድረኩ በሀገራዊ እንዲሁም በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ጉዳዮች ያጠነጠኑ እና በቀጣይ ለሚደረግ ዋና መድረክ የሚቀርቡ አጀንዳዎች የሚለዩበት መሆኑን ጠቁመዋል።
የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ደስታ ዲንቃ በበኩላቸው ከዚህ በፊት በክልሎች በተደረጉ የውይይት መድረኮች የተጠቃለሉ ቁልፍ አጀንዳዎች መነሳታቸውን አስታውሰዋል።
የነበሩት አጀንዳዎች ሀገራዊ ጉዳዮች፣ በመንግስትና በፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም በተፎካካሪ እና በገዥ ፓርቲ የትብብር ማዕቀፍ መዘርጋት፣ በፖለቲካ ምህዳር ማስፋት፣ በሠላምና ደህንነት፣ አካታች ሀገራዊ ምክክርና ሌሎችም ነበሩ ብለዋል።
በመሆኑም በእነዚህና ተያያዥ አጀንዳዎች ዙሪያ የውይይት መድረኩ የሚቀጥል መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።