Fana: At a Speed of Life!

ለ431 የአይሲቲና ዲጂታል ተቋማት የብቃት ማረጋገጫ ፍቃድ ተሰጥቷል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል ለ431 የአይሲቲ እና ዲጂታል የንግድ ተቋማት የብቃት ማረጋገጫ ፍቃድ መሰጠቱን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች የ2016 በጀት አመት ዕቅድ አፈፃፀም እና በ2017 በጀት አመት ዕቅድ ላይ ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)÷ ኢትዮጵያን የዕድገት ጉዞ ለማስቀጠል ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ድርሻ አለው ብለዋል፡፡

ስትራይድ ኢትዮጵያን አጠናክሮ በማስቀጠል ወጣቶች አቅማቸውን እንዲያወጡ መስራት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡

በ2016 በጀት አመት የተሰሩ የስታርትአፕና የምርምር ድጋፍ ስራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ብቻ ሳይሆን ቴክኖሎጂ አምራች ሀይልም መፍጠር ይጠበቅብናል ነው ያሉት።

ከኮርያ መንግስት ጋር በመተባበር በኢኖቤዝ ኬ ኢትዮጵያ በስታርትአፕ ዙርያ ለወጣቶች የተሰጠው ስልጠናና የሚደረገው ድጋፍ እንደ ሀገር በዘርፉ ውጤት ማስመዝገብ የቻለ ነው ተብሏል፡፡

95 የምርመር ተቋማት ተለይተው በተለያዩ ዘርፍ የሚደረጉ ሀገራዊ ምርምሮችን የመደገፍ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝም መገለጹን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

ስትራይድ ኢትዮጵያ ኤክስፖ 2024፣ ስታርትአፕ ኢትዮጵያ ሀገራዊ መድረኮችን በማዘጋጀት ወጣቶች የመደገፍና የማበረታታት ስራ መሰራቱም ተነስቷል።

በቴክኖሎጂ የተደገፈ የመንግስትና የንግድ አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል ከሚሰሩ ስራዎች አንዱ የሆነው የመንግስት የቢዝነስ ፖርታል ላይ በአራት ከተሞች መተግበሩ ለ431 የአይሲቲ እና ዲጂታል የንግድ ተቋማት የብቃት ማረጋገጫ ፍቃድ መሰጠቱ በመድረኩ ተጠቅሷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.