ኮሚሽኑ ለጎፋ ዞን የመሬት መንሸራተት አደጋ ተጎጂዎች የሰብዓዊ ድጋፍ እያደረገ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን በደቡብ ኢትዮጵያ ጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የሰብዓዊ ድጋፍ እያደረገ መሆኑ ተገለጸ።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ከኮሚሽኑ የተገኘውን መረጃ ዋቢ አድርጎ እንዳመለከተው፤ በአደጋው 600 የሚሆኑ ዜጎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል።
የፌደራል መንግስት በኮሚሽኑ በኩል ከ3 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች 520 ኩንታል ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች እርዳታ አቅርቧል።
እያንዳንዱ ጥቅል ለአምስት ሰዎች አገልግሎት የሚሰጡ 100 ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ጥቅሎች ማድረስ መቻሉም ተገልጿል።
በአጠቃላይ 5 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር የሚገመት የሰብዓዊ ድጋፍ መደረጉን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መረጃ አመልክቷል።
ኮሚሽኑ ተጨማሪ የነፍስ አድን ስራው እንዲቀጥልና በአደጋው የስነ-ልቦና ጉዳት የደረሰባቸውም እንዲያገግሙ ከአካባቢው አስተዳደር ጋር በቅንጅት እየሰራ የሚገኝ ሲሆን፤ ወደ ስፍራው የተላከው አጣሪ የጥናት ቡድን ሁኔታውን እያየ ተጨማሪ ድጋፍ የሚያደርግ ይሆናል ተብሏል።