Fana: At a Speed of Life!

ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለ20 ሺህ ዜጎች ነጻ የሕክምና አገልግሎት ሊሰጥ ነው

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በክረምቱ የበጎ ፈቃድ ለ20 ሺህ ዜጎች ነጻ የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀቱን አስታውቋል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በሆስፒታሉ በመገኘት ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።

ሚኒስትሯ በመርሐ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር የጤና ባለሙያዎች በአካባቢ ጥበቃም ይሁን በማህበራዊ ጤና በቅንነት ማገልገል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የሆስፒታሉ ሰራተኞች በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለጌርጌሴኖ የአእምሮ ሕሙማን መርጃ ማእከል የስነ- አዕምሮ ሕክምና ለመስጠት መዘጋጀታቸውን አድንቀዋል።

የበጎ ፈቃድ ሥራ የዘወትር አገልግሎት ሆኖ በመቀጠል አቅመ ደካሞችን፣ ህፃናትና እናቶችን የመደገፍ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልና የጤና ሳይንስ ኮሌጁ በጤናው ዘርፍ የላቀ ሚናቸውን እየተወጡ መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።

በሆስፒታሉ ከዛሬ ጀምሮ “እሺ ለበጎ ተግባር” በሚል መሪ ሃሳብ ለአንድ ወር የሚቆይ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት መደረጉም ተገልጿል።

ሆስፒታሉ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልገሎት ለ20 ሺህ ዜጎች ነፃ የህክምና አገልገሎት ለመስጠት ያቀደ ሲሆን÷ በጌርጌሴኖ የአዕምሮ ሕክምና ማእከል ዘላቂ የሆነ የስነ- አዕምሮ የሕክምና አገልግሎት እንደሚሰጥ ተመላክቷል፡፡

የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በመቄዶንያ የበጎ አድራጎት ማህበር የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በዘላቂነት ዓመቱን ሙሉ እየሰጠ መሆኑ ተጠቅሷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.