የአማራ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔውን ማካሄድ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ጉባዔውን በባህር ዳር ከተማ ማካሄድ ጀምሯል፡፡
ጉባዔውን በንግግር የከፈቱት የክልሉ ዋና አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ፋንቱ ተስፋዬ÷በክልሉ የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ወደ ዘላቂ ሰላም ለማሳደግ ሕዝቡ እያደረገ ያለው ተሳትፎ የሚበረታታ መሆኑን አንስተዋል።
የክልሉ ሕዝብ ወቅታዊ ጥያቄ የሕግ የበላይነት መከበርና ዘላቂ ሰላምን ማስፈን መሆኑን ገልጸው÷ሕዝቡ የሰላም ኮሚቴ አቋቁሞ መንግሥትና የታጠቁ ሃይሎች ተቀራርበው እንዲነጋገሩ የማመቻቸት ሥራ ለመሥራት የሄደበት ርቀት መንግሥት የሚደግፈው ነው ብለዋል።
ክልሉ ባለፈው በጀት ዓመት በጦርነት ውስጥ የቆየ ቢሆንም የክልሉ አስፈጻሚ ተቋማት የልማት ሥራዎች እንዳይቆሙ ያደረጉት ጥረት የሚመሰገን መሆኑንም ገልጸዋል።
በተለይም በአፈር ማዳበሪያ ሥርጭት፣ በገበያ ማረጋጋትና ግጭት በሌለባቸው አካባቢዎች የተከናወነው የመሰረተ ልማት ዝርጋታ አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።
የተጀመረው የፍትሕ ሥርዓት ማሻሻያ በ2017በጀትዓመትም ተጠናክሮ በመቀጠል በስኬት ሊጠናቀቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ምክር ቤቱ ከዛሬ ጀምሮ ለአራት ተከታታይ ቀናት በሚኖረው ቆይታ የ2016 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም፣ የ2017 በጀት ዓመት እቅድና በጀት ማጽደቅ፣ የጠቅላይ ፍ/ቤት፣ የዋና ኦዲተርና የምክር ቤቱን እቅድ አፈጻጸሞች ከመገምገም በተጨማሪ የተለያዩ አዋጆችንና ሹመቶችን ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።
በደሳለኝ ቢራራ