የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ የኢኮ ኢንዱስትሪ ፓርክ እሳቤ አበረታች መሆኑ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ያለው የኢኮ ኢንዱስትሪ ፓርክ እሳቤ አበረታች መሆኑን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሰሀ ይታገሱ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ዋና ስራ አስፈፃሚው የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክን ወቅታዊ የስራ እንቅስቃሴ ተመልክተዋል።
በኢንዱስትሪ ፓርኩ የሚገኙ አምራች ኩባንያዎችን ጎብኝተው ከሀገር በቀልና ከውጪ ኢንቨስተሮች ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም አምራች ኩባንያዎች ስላሉበት የምርት እንቅስቃሴ፣ የስራ እድል ፈጠራ፣ የወጪ ምርት እና የተኪ ምርት ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችና አፈፃፀሞች ላይም አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡
የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለኢንቨስተሮች ያለው ምቹ ከባቢያዊ ሁኔታ እና በፓርኩ ለኢኮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት የተሰሩ የአረንጓዴ ልማት ስራዎች ሀገራዊውን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የሚያግዙ መሆናቸው ተገልጿል።
በኢንዱስትሪ ፓርኩ ከነበረው ፕሮግራም ጎን ለጎን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርም ተከናውኗል።