የአደይ አበባ ስታዲየም በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ ይገባል – ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአደይ አበባ ስታዲየም ግንባታ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ተከናውኖ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ ይገባል ሲሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ተናገሩ፡፡
ሚኒስትሯ በአደይ አበባ ስታዲየም በመገኘት የስታዲየሙን አጠቃላይ የሥራ አፈጻጸምና ሒደት በመገምገም የሥራ አቅጣጫ ሰጥተዋል።
በዚህ ወቅትም በስታዲየሙ የግንባታ ሥራ ውስጥ ለአሰራር ምቹ ያልሆኑ እና ለፕሮጀክቱ አፈጻጸም ተግዳሮት ለሆኑ ችግሮች አስቸኳይ መፍትሔ መስጠት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ስታዲየሙ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ተገንብቶ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ ይገባል ያሉት ሚኒስትሯ ÷ የውጭ ምንዛሬ የማይጠይቁና በሀገር ውስጥ ተቋራጮች መከናወን የሚችሉ ሥራዎች ተለይተው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡
በታሕሳስ 2008 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው የአደይ አበባ ስታዲየም 62 ሺህ ሰዎችን የመያዝ አቅም ያለው ሲሆን፥ የስታዲየሙ መጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ መጠናቀቁ ይታወቃል።
የስታዲየሙ የ2ኛ ምዕራፍ ግንባታ ጣሪያ ማልበስ፣ ወንበር መግጠም፣ የሰው ሰራሽ ሃይቅ ግንባታ፣ ዘመናዊ የደህንነት ካሜራ መግጠም፣ የድምጽ ሥርዓት መዘርጋት፣ የፓርኪንግ ቦታዎችና ሌሎች ሥራዎችን መያዙ ተጠቁሟል፡፡
ከጉብኝቱ በተጨማሪ በስታዲየሙ የሁለተኛ ምዕራፍ ግንባታ ሒደት ዙሪያ ውይይት መደረጉንም የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡