Fana: At a Speed of Life!

ፓኪስታን በጎፋ ዞን የመሬት መንሸራተት ባደረሰው ጉዳት ሐዘኗን ገለፀች

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ፓኪስታን በጎፋ ዞን የተከሰተው የመሬት መንሸራተት ባስከተለው ጉዳት የተሰማትን ሐዘን በመግለጽ ከኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ጎን መሆኗን አስታወቀች፡፡

ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ግለሰቦች፣ የፓርላማ አባላት፣ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ እና የሐይማኖት መሪዎች፣ የንግድና የመገናኛ ብዙኃን፣ ወጣቶች እና የሲቪክ ማኅበራት በኢስላማባድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተገኝተው ሐዘናቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚሁ መሠረት የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር የአየር ንብረት ለውጥ አማካሪ ሮሚና ኩርሺድ አላም፣ ሴናተር ሙሻሂድ ሁሴን፣ በፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዳይሬክተር ጄኔራል ሃስናይን የሱፍ፣ የፓኪስታን የፕሬስ ካውንስል ሊቀ መንበር አርሻድ ካን ጃዶን፣ የተህሪክ-ኢ-ጃዋና ፓኪስታን ሊቀ መንበር መሀመድ አብዱላህ ሃሚድ ጉል፣ በኢስላማባድ የንግድ ምክር ቤት ሊቀ መንበር አህሳን ዛፋር ባክታዋሪ የተመራ ልዑክ እና የፓኪስታን አፍሪካ ወዳጅነት ማኅበር ሊቀ መንበር ዛፋር ባክታውሪ በኤምባሲው ተገኝተው ሐዘናቸውን ገልጸዋል፡፡

በተዘጋጀው የሐዘን መዝገብ ላይ ፊርማቸውን ማኖራቸውንም የኤምባሲው መረጃ አመላክቷል፡፡

አምባሳደር ጀማል በከር በበኩላቸው መንግስት ተጎጂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም እያደረገ ያለውን የዕርዳታ እና ድጋፍ ሥራ እንዲሁም ከአረንጓዴ ዐሻራ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ እያከናወነች ስላለው ተግባር ከአስረድተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.