በሀገራዊ ምክክሩ የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎና ሚና ላይ ያተኮረ መድረክ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎና ሚና ላይ ያተኮረ 2ኛ ዙር ሀገር አቀፍ የምክክር መድረክ በሐዋሳ ከተማ እያካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ የኢትይጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ (ዶ/ር)÷ ኮሚሽኑ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ሀገሪቱ በሚያጋጥሟት ግጭቶች ግንባር ቀደም ተጎጂ የሆኑት አካል ጉዳተኞች ችግሮችን በውይይት ለመፍታት በሚደረገው ሂደት ትርጉም ያለው ተሳትፎ ሊያደርጉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በመሆኑም በምክክሩ አካል ጉዳተኞች አጀንዳቸውን ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከማሳወቅ ባሻገር በሂደቱ በባለቤትነት መሳተፍ እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ በበኩላቸው÷ በሚፈጠሩ አለመግባባቶችና ግጭቶች አካል ጉዳተኛው የከፋ ጉዳት እንደሚያጋጥመው ጠቅሰዋል።
ችግሮችን በምክክር በመፍታት ሂደት የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው፤ የአካል ጉዳተኞች ተወካዮች ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ አስገንዝበዋል።
ችግሮችን በዴሞክራሲያዊ መንገድ በውይይት የመፍታት ባህልን ማዳበር እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
በሀገራዊ ምክክሩ የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎና ሚና ዙሪያ በሚካሄደው መድረክ ከክልሎች፣ ከከተማ አስተዳደሮች፣ ከተለያዩ የአካል ጉዳተኞች ማህበራትና ከአካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን የተወጣጡ ተወካዮች እየተሳተፉበት እንደሚገኙ የምክክር ኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡