የአፍሪካን የቡና ልማት ጥራትና ግብይት ለማሳደግ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል – ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካን የቡና ልማት ጥራትና ግብይት ለማሳደግ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ሲሉ የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የካምፓላ ዲክላሬሽን በአፍሪካ ሕብረት መጽደቁን አስመልክቶ ዛሬ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል።
የድርጅቱ ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ÷ ኢትዮጵያም ድርጅቱን በሊቀመንበርነት የመምራት ዕድል ማግኘቷ የቡናን እድገት ለማምጣት ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
ድርጅቱ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ቡና እንዲያመርቱ ዕድል እንደሚሰጥ በመግለጽ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የአቅም ማጎልበቻ ማዕከል ለማድረግ በሂደት ላይ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
በኢትዮጵያ ቡና ከጠቅላላው የወጪ ገቢ ንግድ 36 በመቶ እንደሚይዝ የገለጹት ሚኒስትሩ ÷ ከቡና ምርት 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ማግኘቷንና ይህም ካምናው የ20 በመቶ ብልጫ እንዳለው ጠቁመዋል።
የአፍሪካ ሕብረት የግብርናና ገጠር ልማት ኮሚሽነር አምባሳደር ጆሴፋ ሊኦኔል በበኩላቸው ÷ የአፍሪካ ሕብረት ቡናን አጀንዳ አድርጎ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የቡናን ምርትና ምርታማነት ከማሳደግ ባሻገር የአፍሪካ ዜጎቸን በእሴት ሰንሰለት ጭማሪ በማሳተፍ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየተሰራ እንደሆነም ነው ያነሱት።
በአፍሪካ 25 ሀገራት ቡና አምራች መሆናቸውን ኮሚሽነሯ ጠቅሰው ÷ 17 በመቶ የአፍሪካ ሕዝብ በቡና እንደሚተዳደር መናረቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የአፍሪካ ቡና ድርጅት ዋና ጸሐፊ አምባሳደር ሰለሞን ሩቴጋ ÷ የአፍሪካ የቡና ምርት ለማሳደግ የማስተዋወቅ፣ በምርምር የመደገፍ፣ የግል ዘርፉን በስፋት የማሳተፍና የፈጻሚዎችን አቅም ለማጎልበት ስትራቴጂክ እቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል፡፡