Fana: At a Speed of Life!

መንግሥት ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራ የገባው በበቂ ዝግጅት ነው – ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግሥት ቀጣይነት ያለው እድገት ለማስመዝገብና የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በማለም የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራ የጀመረው በጥናት ላይ የተመሰረተ በቂ ዝግጅት አድርጎ መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ።

ኢትዮጵያ ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራ መግባቷን አስመልክቶ ሚኒስትሯ በሰጡት መግለጫ፤ በኢትዮጵያ የነበረው ተጨባጭ የኢኮኖሚ ሁኔታ ሀገሪቱ ያሰበችውን እድገት ለማሳካት የማያስችል በመሆኑ የለውጡ መንግሥት ይህንን ለመቀየር የመጀመሪያውን ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ ማድረጉን አስታውሰዋል።

በወቅቱ የሀገር ውስጥ ገቢና ከውጭ የሚገባው ፋይናንስ አነስተኛ መሆን፣ ዝቅተኛ የፕሮጀክት የመፈጸም አቅም፣ የፖሊሲ ማነቆዎችን ጨምሮ መዋቅራዊ ችግሮች፣ የግሉ ዘርፍ የኢኮኖሚው መሪ አለመሆን፣ የምርታማነት ማነስና የሥራ እድል ፈጠራ መቀዛቀዝ የኢኮኖሚው ዋነኛ መግለጫዎች እንደነበሩ ገልጸዋል።

ይህንን ችግር ለማቅለል ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በመቅረጽ ወደ ሥራ መገባቱን ጠቅሰው፤ በተለይም በመጀመሪያ ምዕራፍ በሦስት ምሦሦዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ተጨባጭ ለውጥ መጥቷል ብለዋል።

በዋናነትም በማክሮ ፋይናንስ ዘርፍ የፊስኪል ፖሊሲ (የመንግሥት ወጪና ገቢን) በተመለከተ የመንግሥት ገቢ አስተዳደርን በማዘመን ለውጥ ማምጣት መቻሉን ጠቅሰዋል።

የመንግሥት ወጪን በማስተዳደር በተለይም ኢንቨስትመንት እንዲሻሸልና ፕሮጀክቶች በታለመላቸው የጊዜ ገደብ፣ ጥራትና ገንዘብ እንዲጠናቀቁ በማድረግ ከፍተኛ ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል።

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የነበረባቸውን ሥር የሠደደ መዋቅራዊ ችግር በመፍታት ትርፋማ መሆን መቻላቸውን ገልጸው፤ የንግድ ብድርን ሙሉ በሙሉ በማስቀረትና የእዳ ክምችትን በመቀነስ ረገድ ትልቅ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።

በመዋቅራዊ ዘርፍም በርካታ የሕግ ማዕቀፎችን በማሻሻል፣ የንግድና የኢንቨስትመንት ከባቢ ምቹ በማድረግ፣ እንዲሁም ምርታማነትን በማሳደግና ተወዳደሪነትን በመፍጠር እመርታ ታይቷል ብለዋል።

በመጀመሪያው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ መሻሻያ የተገኙ ስኬቶችን ለማስቀጠልና ችግሮችን ለመፍታት መንግሥት ወደተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራ መግባቱን ጠቅሰው፤ ውሳኔው ወቅታዊና ኢትዮጵያ ለምታልመው ብልጽግና ምቹ መደላልድል የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።

ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራ ለመግባት ላለፉት አምስት ዓመታት ከሀገር ውስጥና ከውጭ ባለሙያዎች ጋር በመሆን ጥናት መደረጉን ጠቅሰው፤ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተጓዳኝ ተጽዕኖዎችን ለመቀነስ ሊወሰዱ የሚገቡ እርምጃዎችም በጥናት ተመላክቷል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራ በአራት ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥንና አሁንም ሀገሪቱን እየፈተኑ ያሉ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በመፍታት በሂደት ተገማችና የተረጋጋ የማክሮ የኢኮኖሚ ሁኔታ እንዲኖራት ያስችላል ሲሉ ተናግረዋል።

በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ የዋጋ መዛባትን በማስተካከል፣ ምርታማነትን በመጨመር፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በማጠናከር፣ የውጭ ሓዋላን በማሳደግ፣ ሕገ-ወጥና የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴዎችን በመግታት ተጨባጭ ለውጥ ያመጣል ብለዋል።

የሀገሪቱን የማኅበራዊ ልማት ሥራዎችን በማሳለጥ በድኅነት ቅነሳ ላይ ተጨባጭ አዎንታዊ ለውጥ እንደሚያመጣም አስረድተዋል።

ሲንከባለሉ የመጡ ሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራው እንቅፋት እንዳይሆኑ በተለይም የተቋማት ሪፎርም መጀመሩን ጠቅሰው፤ ተቋማት በብቁ ባለሙያዎች እንዲደራጁ የማድረጉ ሥራ ተጀምሯል ብለዋል።

የመንግሥት አገልግሎቶች በዲጂታል ሥርዓት እንዲደገፉ የተጀመረው ሥራ ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ማረጋገጣቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

የማሻሻያ ትግበራው በተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳያሳደር ዝቅተኛ የደሞዝ ተከፋይ ለሆኑ የመንግሥት ሠራተኞች የደሞዝ ጭማሪ በማድረግ ተጓዳኝ አሉታዊ ጫናዎችን ለመቋቋም ጥረት እንደሚደረግ ዶክተር ፍጹም ተናግረዋል።

በተጨማሪም ልማታዊ የሴፍቲኔት መርሐ ግብር እንደሚጠናከርና እንደ ነዳጅና ማዳበሪያ በመሰሉ ሸቀጦች ላይ ድጎማ እንደሚያደረግ ጠቁመዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.