አቶ ሽመልስ አብዲሳ በሊበን ወረዳ የስንዴ ሰብል ምርት ማሰባሰብ ስራን አስጀመሩ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በክልሉ ምስራቅ ቦረና ዞን ሊበን ወረዳ የለማውን የስንዴ ሰብል ምርት ማሰባሰብ ስራ አስጀመሩ።
አቶ ሽመልስ አብዲሳ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት፤ አካባቢው በሚያጋጥመው ተደጋጋሚ ድርቅ በሴፍቲኔት ሲረዳ የቆየ መሆኑን አስታውሰው፤ አሁን እየተሰራ ባለው ስራ ከተረጅነት መላቀቅ ችሏል ብለዋል።
በዞኑ የታየው ውጤት ኢትዮጵያ ከተረጅነት ለመውጣት የምታደርገው ጥረት እውን እንደሚሆን ትልቅ ማሳያ ነው በማለት ገልጸው፤ የአካባቢው አርሶና ከፊል አርብቶአደር የምግብ ዋስትናውን ከማረጋገጥ አልፎ የቁጠባ ባህሉን በማዳበር ኢኮሚያዊ ተጠቃሚነቱን ማረጋገጥ መቻሉን ተናግረዋል።
ዝናብ አጠር በሆኑ የክልሉ ቆላማ አካባቢዎች የሚያጋጥመውን ድርቅና ተያያዥ ማህበራዊ ተግዳሮት ለመፍታት የፊና ግድብ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ ሌሎች ስራዎች በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዞኑ በተለያዩ ሰብሎች ከለማው ከ141 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ውስጥ 71 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ ሰብል የተሸፈነ መሆኑ ተመላክቷል።
የስንዴ ሰብሉ ምርታማነትን ለማሳደግ በሚያስችል መልኩ በኩታ ገጠም የእርሻ ዘዴ የለማ መሆኑ ተነግሯል።
በአጠቃላይ ከ2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ ወደ ምርት ስብሰባ ሂደት መገባቱን የዞኑ ግብርና ፅ/ቤት ኃላፊ መስቀሉ ቱሉ ተናግረዋል።
የስንዴ ሰብል ምርት ማሰባሰብ መርሐ ግብሩ ማስጀመር ላይ በብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ኃላፊ ፍቃዱ ተሰማ፣ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ፣ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) እና ሌሎችም የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በመራኦል ከድር