ዶ/ር መቅደስ የወባ በሽታ ምላሽ አሰጣጥ ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳሰቡ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) እየተከናወነ የሚገኘው የተቀናጀ የወባ በሽታ የምላሽ አሰጣጥ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ አሳሰቡ፡፡
የወባ በሽታ መከላከል እና መቆጣጠር የተቀናጀ የምላሽ አሰጣጥ ሥራዎች ላይ የመረጃ ልውውጥና የውይይት መድረክ ተካሂዷል፡፡
ዶ/ር መቅደስ÷የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ህብረተሠብ ጤና ኢንስቲትዩት ከሁሉም ክልሎች ጋር በመተባባር እያከናወኑት የሚገኘው የተቀናጀ የወባ በሽታ ምላሽ አሰጣጥ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
የወባ በሽታን በተመለከተ መረጃን በየእለቱ በማረጋገጥና የመረጃ ጥራትን በማሻሻል ለህብረተሠቡ ትክክለኛ መረጃ ማድረስ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በግጭት አከባቢዎች የድንገተኛ ምላሽ አሰጣጥ አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ ላይ በትኩረት እንዲሠራ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ጤና ኬላዎችን ሥራ በማስጀመር የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች የወባ በሽታን አካትተው እንዲሰሩ ማድረግ እንደሚገባ መናገራቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡