የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአዳዲስ ታክስ ሕጎች ትውውቅ መድረክ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ የበጀት ዓመቱን አፈጻጸምና የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ዝግጅት እና የታክስ ሕጎች የትውውቅ መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡
በመድረኩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎችና ባላድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ÷ክልሉ የተሻለ የገቢ ምንጭ ባለቤት በመሆኑ ያለውን የገቢ አቅም በሚገባ በመሰብሰብ ለልማት ማዋል ይገባል ብለዋል።
የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ሃላፊ ወ/ሮ አለምነሽ ደመቀ በበኩላቸው÷በክልሉ የሚገኙትን የገቢ አማራጮች አሟጦ በመጠቀም በ2017 ዓ.ም ከ21 ቢሊየን ብር በላይ ለመሰብሰብ እቅድ ተይዞ ወደ ተግባር መገባቱን ተናግረዋል፡፡
መድረኩ የቢሮውን የ2016 በጀት ዓመት አጠቃላይ የሥራ አፈጻጸም በመገምገም የነበሩ ጥንካሬዎች፣ የተገኙ ስኬቶችንና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በመለየት በጥልቀት ይወያያል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በተጨማሪም በክልሉ መስተዳድር ም/ቤት የጸደቁ አዳዲስ የታክስ ሕጎች ትውውቅ የሚደረግ ሲሆን÷ የቢሮው የ2017 በጀት ዓመት ጠቋሚ መነሻ ዕቅድ ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግበትም ተጠቁሟል፡፡
በመድረኩ ለቀጣይ የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ዝግጅትና ለተሻለ ውጤታማ አፈጻጸም የሚሆን ግብዓት በማዳበር ጥቅም ላይ የሚውል መሆኑም ተጠቅሷል፡፡
በታሪክነሽ ሴታ