ስታርትአፖችን ማስተናገድ የሚያስችል ሥነ-ምሕዳር ለመገንባት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ስታርትአፖችን በአግባቡ ማስተናገድ የሚያስችል ሥነ-ምሕዳር ለመገንባት በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡
በኢትዮጵያ የስታርትአፕ ሥነ-ምህዳርን ምቹ ለማድረግ እየተዘጋጀ ባለው ረቂቅ አዋጅ ዝርዝር ይዘት ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በውይይቱ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)፣ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) እና የሁለቱ ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
የስታርትአፕ ረቂቅ አዋጅ ለማዘጋጀት የሚያስችሉ ግብዓቶች በኢትዮጵያ ስታርትአፕ ኤግዚቢሽን እና ሌሎች መድረኮች የተሰበሰቡ ሲሆን÷ ዝርዝር ጉዳዮችን አስመልክቶ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይቶች እየተካሄዱ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
በለጠ ሞላ (ዶ/ር)÷ የሰውን አኗኗር ለማቅለል እና ችግሮችን ለመፍታት የሚፈጠሩ ስታርትአፖች የሚደገፉበት የአሰራር ስርዓት እና ሕግ ማዕቀፎችን ለመዘርጋት በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡
የስታርትአፕ ሥነ ምህዳር ግንባታው በተጠናከረ መንገድ እንዲከናወን እና የሚፈለገውን ውጤት እንዲያስመዘግብ የሚዘጋጁ የሕግ ማዕቀፎች ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መወያየት ተገቢ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ይህንን በመገንዘብም መንግስት ስታርትአፖችን በአግባቡ ማስተናገድ የሚያስችል ሥነ-ምህዳር ለመገንባት በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል፡፡
በረቂቁ አንደአዲስ የተካተቱ እና የተሻሻሉ ጉዳዮች ዙሪያ በጥልቅት ውይይት የተደረገ ሲሆን÷ በዋናነት የስታርትአፕ ስያሜ፣ የግራንት፣ ፈንድ ኦፍ ፈንድ እና የብድር ዋስትና ጉዳዮች ላይ መግባባት ላይ መደረሱን የሚኒስቴሩ መረጃ አመልክቷል፡፡