Fana: At a Speed of Life!

አሜሪካና ብሪታኒያ በሁቲ አማጺያን ይዞታዎች ላይ ጥቃት ፈፀሙ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ እና ብሪታኒያ የሁቲ አማፂያን ላይ ያነጣጠረ ወታደራዊ ጥቃት መፈፀማቸው ተገለፀ፡፡

የአማጺ ቡድኑ የመረጃ ምንጭ የሆነው አል ማሲራህ የዜና ምንጭን ጠቅሶ አረብ ኒውስ እንደዘገበው፤ ቡድኑን ዒላማ ያደረገው ሁለት ተከታታይ ጥቃት የተፈጸመው በደቡብ ምዕራብ የመን በምትገኘው ቴዝ ከተማ ነው፡፡

ሀገራቱ የፈጸሙት የተቀናጀ ጥቃት አማፂያኑ በቀይ ባህር ላይ በሚገኙ ዓለም ዓቀፍ የንግድ መስመሮች ላይ ለሚፈፅሙት ጥቃት ምላሽ መሆኑ ነው የተገለፀው፡፡

ቀደም ሲል በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኘው የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ በሁቲ አማጺያን የተወነጨፉ ድሮኖች እና ሁለት ባለስቲክ ሚሳኤሎችን ማወደሙን የገለፀ ሲሆን፤ በዛሬው እለት ደግሞ ሀገራቱ አማፂያኑ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ፈጽመዋል፡፡

የሁቲ አማጺያን የጋዛ ጦርነት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በቀይ ባህር፣ በባብ ኤል-መንደብ ሰርጥ፣ በኤደን ባህረ ሰላጤ እና በህንድ ውቅያኖስ ላይ በሚተላለፉ የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት ሲፈፅሙ ቆይተዋል፡፡

አማፂያኑ ባወጡት ወታደራዊ መረጃ ከሕዳር ወር ጀምሮ በፈፀሙት ጥቃት 42 የእስራኤል፣ 72 የአሜሪካ፣ 12 የእንግሊዝ እና 45 የሌሎች ሀገራት በአጠቃላይ 172 የንግድ መርከቦችን ማውደማቸውን ገልፀዋል፡፡

ጥቃቱን የሚፈፀሙት በጋዛ ጦርነት ለፍልስጤም ድጋፋቸውን ለማሳየት መሆኑን የገለፁት የሁቲ አማጽያን፤ እስራኤል ጦርነቱን የማታቆም ከሆነ በቀይ ባህር በሚንቀሳቀሱ መርከቦች ላይ ጥቃት መፈፀማቸውን እንደሚቀጥሉ ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.