Fana: At a Speed of Life!

ኮርፖሬሽኑ አዳዲስ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ ከሚኒስቴሩ ጋር እንደሚሰራ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢንዱስትሪ ፓርኮች ያለውን አዳዲስ የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት ለማሳደግ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በትብብር እንደሚሠራ ተገለጸ፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሰሐ ይታገሱ (ዶ/ር) ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ጋር በኢንዱስትሪ ፓርኮች ያለውን የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡

በዚሁ ወቅትም የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመትን ለመሳብ፣ ገበያ ለማፈላለግ፣ በፋርማሲዩቲካል፣ በኃይቴክ፣ በጨርቃጨርቅና አልባሳት፣ በግብርና ምርቶች ማቀነባበር እና ተያያዥ ኢንቨስትመንቶች ላይ ከፍተኛ ልምድና አቅም ያላቸው አዳዲስ የውጭ ኢንቨስተሮች በፓርኮችና በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ኢንቨስት እንዲያደርጉ በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ቆንፅላዎች ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ አድርገው እንዲሠሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጠይቀዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑም የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት በአሠራርና አደረጃጀት ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን አረጋግጠዋል፡፡

አምባሳደር ምስጋኑ በበኩላቸው በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚገኙ መሰረተ ልማቶች ለኢንቨስትመንት ምቹ አጋጣሚ በመሆናቸው አሟጥጦ መጠቀም እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

ተቋማቸውም ኮርፖሬሽኑን ጨምሮ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር በመስራት የተለያዩ ዓለም አቀፍ ባዛርና ዐውደ-ርይዮችን በማዘጋጀት በዘርፉ ያሉ መልካም አጋጣሚዎችን ይበልጥ ለመጠቀም በቅንጅት ይሠራል ብለዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.