ከፀጥታ አካላት ጋር የሠራንባቸው የፈተና አሰጣጥ ሂደቶች የሚበረታቱ ናቸው- ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከፀጥታና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በሠራንባቸው ባለፉት ሦስት ዓመታት የፈተና አሰጣጥ ሂደቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መጥቷል ሲሉ የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ገለጹ፡፡
የ2016 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና አፈፃፀም ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተገምግሟል፡፡
በዚሁ ወቅት ሚኒስትሩ እንዳሉት ከፀጥታና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በሠራንባቸው ባለፉት ሦስት ዓመታት የፈተና አሰጣጥ ሂደቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መጥቷል፡፡
በተለይም የሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር የፈተናውን ሂደት ሰላማዊ እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከተው የፀጥታ ኃይል የላቀ ምስጋና ይገባዋል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና እንዳይካሄድ ቅስቀሳ ሲያደርጉ የነበሩ የሽብርና የፅንፈኛ ቡድኖችን ሴራ በማክሸፍ ፈተናው ከህትመት ጀምሮ ወደ መፈተኛ ጣቢያዎች ሲጓጓዝ በማጀብና በዩኒቨርሲቲዎችም ከፍተኛ ጥበቃ አድርጓል ብለዋል፡፡
ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የዩኒቨርሲቲ ፖሊስ ጥበቃ መምሪያን የሪፎርሙ አንዱ አካል አድርጎ በማቋቋሙ የመማር ማስተማር ሂደቱ ሰላማዊ እንዲሆን ከፍተኛ ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡