Fana: At a Speed of Life!

ሕንድ በጤናው ዘርፍ የምታደርገውን ድጋፍ እንደምታጠናክር ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በኢትዮጵያ የሕንድ አምባሳደር አኒል ኩማር ከተመራ ልዑክ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም÷ሀገራቱ በተለያዩ የጤና ዘርፎች ዙሪያ በትብብር መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል፡፡

ዶ/ር መቅደስ ኢትዮጵያና ሕንድ ያላቸው ዘርፍ ብዙ ግንኙነት በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረና በተለይ በጤናው ዘርፍ ያለው ትብብር የሚያበረታታ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ትብብሩን ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ ሚኒስቴሩ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸው÷በሀገር ውስጥ የሕክምና ግብዓቶችን ለማምረት በሚደረገው ጥረት የሕንድ ተቋማት በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አምባሳደር አኒል ኩማር በበኩላቸው÷በታወቁ የሕንድ ዩኒቨርሲቲዎች ለኢትዮጵያውያን የጤና ባለሙያዎች ስልጠና ለመስጠት መንግስታቸው ሁኔታዎችን እያመቻቸ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሰው ስራሽ አካልና የአካል ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው በርካታ ዜጎች የሕንድ መንግስት ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰው÷በቀጣይ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ከሕንድ ባለሃብቶች ጋር የሕክምና መሳሪያዎችን፣ መድኃኒቶችንና ግብዓቶችን ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በዘርፉ ተሰማርተው ማምረት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ እንደሚወያዩ መጠቆማቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ አመልክቷል፡፡

ሕንድና ኢትዮጵያ ያላቸው ግንኙነት እጅግ በርካታ ዘመናትን ያስቆጠረ መሆኑን አውስተው÷ይህንን ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ አበክረው እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.