ቻይና በአዲስ አበባ የቻይና-አፍሪካ ጂኦ ሳይንስ ማዕከል መክፈት እንደምትፈልግ ገለጸች
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ኢጃራ ተስፋዬ ከቻይና ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ፕሬዚዳንት ሊ ጂንፋ (ዶ/ር) ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም÷ በጂኦሎጂካል ሰርቬይ ዘርፍ በትብብር መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩትና የቻይና ጂኦሎጂካል ሰርቬይ የቆየ ግንኙነት እንዳላቸውና ውጤታማ ሥራዎችን በትብብር ማከናወናቸው ተጠቁሟል፡፡
በቀጣይ በጂኦ ሳይንስ፣ በጂኦሎጅ ማፕና በጂኦ ኬሚካል ማፕ እንዲሁም በማዕድን ፍለጋና በአቅም ግንባታ ዙሪያ በትብብር ለመስራት ዝግጁ እንደሆኑ መገለጹን የኢንስቲትዩት መረጃ አመልክቷል፡፡
የቻይና ጂኦሎጂካል ሰርቬይ በአዲስ አበባ የቻይና-አፍሪካ የጂኦ ሳይንስ ማዕከል ለመክፈት ፍላጎት እንዳለውና ከኢንስቲትዩቱ ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚፈልግም አስታውቋል፡፡