በአፍሪካውያን ባለሃብቶች የሚመሩ የማምረቻ ማዕከላት አህጉራዊ ትስስርን ያሳድጋሉ – ዋምኬሌ ሜኔ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፍሪካውያን ባለሃብቶች የሚመሩ የማምረቻ ማዕከላት አህጉራዊ ትስስርን እንደሚያሳድጉ የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጣና ሴክሬታሪያት ዋና ጸሐፊ ዋምኬሌ ሜኔ ገለጹ፡፡
ዋምኬሌ ሜኔ እና ልዑካቸው ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ጋር በመሆን የ”ኤኤምጂ” ሆልዲንግስ የማምረቻ ኮምፕሌክስን ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸውም÷ የኮምፕሌክሱን የማምረት ሒደትና በቅርቡ ወደ ማምረት የሚገቡ የአዳዲስ ፋብሪካዎችን ግንባታ ተመልክተዋል፡፡
ግንባታዎቹ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የማኑፋክቸሪንግ ማዕከል ለማድረግ የተጀመረው ሥራ ወደ አንድ ከፍታ መድረሱን የሚያሳይ እንደሆነ መገንዘባቸውን ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ዋምኬሌ ሜኔ በበኩላቸው÷ መሰል በአፍሪውያን ባለሃብቶች የሚመሩ የማምረቻ ማዕከላት የአህጉሪቱን የእርስ በርስ የንግድ ትስስር ማሳለጥ እንደሚያስችሉ አመልክተዋል፡፡