Fana: At a Speed of Life!

በአዲሱ ዓመት የኢትዮጵያ ጓዳዎች በበረከት እንዲሞሉ የተጀመረው ውጤታማ ጉዞ ተጠናክሮ ይቀጥላል – አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መጪው አዲስ አመት የኢትዮጵያ ጓዳዎች በበረከት የተትረፈረፉ ይሆኑ ዘንድ የጀመርነውን የውጤታማነት ጉዞ አጠናክረን እንቀጥል ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለፁ፡፡

አቶ አደም ፋራህ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ፥ በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች በግብርናው ዘርፍ እየታዩ ያሉ ውጤቶች ተስፋ ሰጪ ናቸው ብለዋል፡፡

የገበሬዎቻችን የድካም ፍሬ፣ የአመራራችን ትኩረት፣ የግብርና ባለሙያዎቻችን ጥረት እንዲሁም የምድራችን ተፈጥሮ ለጋስነት በአንድ ላይ ተደማምረው የያዝነውን ክረምት እሸታማ አድርገውታል ነው ያሉት።

በቆሎው፣ስንዴው፣ ጤፉ፣አኩሪ አተሩ፣ ቦሎቄው፣ አገዳው፣ ሩዙ ፍራፍሬው ቅመማ ቅመሙ እንዲህ ባማረ መልኩ የምርታማነታችን መገለጫ ሆኖ፣ በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች ፓርቲያችን በብዝሃ ዘርፍ የኢኮኖሚ አቅጣጫው ለግብርናው ዘርፍ በሰጠው ልዩ ትኩረት ምክንያት አስደማሚ ውጤት እየተመዘገበ ይገኛል ሲሉም ገልጸዋል።

አክለውም ፥ በምግብ ራሳችንን ለመቻል የምናደርገው ጥረት ሙሉ ለሙሉ ሊሳካ እንደሚችል፣ ከሰራን እና ሌት ከቀን ከለፋን ድሉ የእኛ እንደሆነ የኢትዮጵያ የዘንድሮ የምርት ጊዜ አበይት ምስክር መሆን ይችላል ብለዋል፡፡

“የእሸቱ ጊዜ እንዳማረ የአጨዳው ጊዜም ይመርልን ነውና ብሒሉ” በድንገተኛ የተፈጥሮ ክስተት የደረሱ ሰብሎች፣ አዝርቶች እና ፍራፍሬዎች ጉዳት እንዳይደርስባቸው ጥንቃቄ እናድርግ ሲሉም አሳስበዋል፡፡

ሰማዩን ቀድሶ ምድሩን አለስልሶ ለሰጠን ፈጣሪ ምስጋና እያቀረብን ፤ መጪው አዲስ ዓመት የኢትዮጵያ ጓዳዎች በበረከት የተትረፈረፉ ይሆኑ ዘንድ የጀመርነውን የውጤታማነት ጉዞ አጠናክረን እንቀጥል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.