Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ በ24 ሰዓታት 141 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ሲገኝባቸው የ3 ሰዎች ህይወት አልፏል

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ በተደረገው 4 ሺህ 675 የላብራቶሪ ምርመራ 141 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 5 ሺህ 175 መድረሱንም የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ዛሬ ባወጡት ሪፖርት አመላክተዋል።

ቫይረሱ በምርመራ ከተገኘባቸው ሰዎች ውስጥ 139 ኢትዮጵያውያን፤ 2 ሰዎች የውጭ ዜጎች ሲሆኑ፥ የእድሜ ክልላቸውም ከ2 ወር እስከ 87 ዓመት የሆኑ 81 ወንዶች እና 60 ሴቶች ናቸው።

ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች መካከልም 113 ሰዎች ከአዲስ አበባ፣ 15 ሰዎች ከኦሮሚያ ክልል፣ 6 ሰዎች ከሐረሪ ክልል፣ 3 ሰዎች ከጋምቤላ ክልል፣ 2 ሰዎች ከሶማሌ ክልል፣ 1 ሰው ከድሬ ደዋ ከተማ አስተዳደር እና 1 ሰው ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ናቸው።

ከዚህ ባለፈ 3 በህክምና ማዕከል ውስጥ በህክምና ላይ የነበሩ ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን፥ ህይወታቸው ያለፈውም የ52 እና 72 ዓመት ወንዶች እና የ62 ዓመት ሴት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ናቸው።

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ቫይረሱ የተገኘባቸው እና ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 81 መድረሱን በመግለፅ፤ በህልፈተ ህይወታቸው የተሰማቸውን ሀዘን ገልፀው ለቤተሰቦቻቸው መፅናናትን ተመኝተዋል።

በሌላ መልኩ በትላንትናው 58 ሰዎች (44 ከአዲስ አበባ፣ 8 ከኦሮሚያ ክልል፣ 3 ከሶማሊ ክልል፣ 2 ከደቡብ ክልል እና 1 ከትግራይ ክልል) ያገገሙ ሲሆን፥ በአጠቃላይ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 1 ሺህ 544 ደርሷል።

ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ እስካሁን ለ232 ሺህ 50 ሰዎች ምርመራ የተደረገ ሲሆን፥ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 5 ሺህ 175 ደርሷል።

አሁን ላይ ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች ቁጥር 3 ሺህ 548 ሲሆን፥ ከእነዚህም ውስጥ 30 ሰዎች በጽኑ የታመሙ መሆናቸውንም የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

እስካሁን በኢትዮጵያ 1 ሺህ 544 ሰዎች ከቫይረሱ ሲያገገሙ፤ የ81 ሰዎች ህይወት አልፏል፤ 2 ሰዎች ወደ ሀገራቸው መመለሳቸው ይታወሳል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.