Fana: At a Speed of Life!

የጳጉሜን ቀናት በተለያየ ዝግጅት ይከበራሉ- አገልግሎቱ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የ2017 ዓ.ም አዲስ ዓመት ዋዜማ አምስቱ የጳጉሜን ቀናት በሀገር ዓቀፍ ደረጃ በተለያየ ዝግጅትና ስያሜ ለማክበር ዝግጅት መጠናቀቁን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡

የአገልግሎቱ ሚኒስትር ዴዔታ ከበደ ዴሲሳ በሰጡት መግለጫ÷ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የጳጉሜን ቀናት የዜጎችን አንድነትና አብሮነት በሚያጎላ መልኩ መከበራቸውን አስታውሰዋል።

በዘንድሮው የ2017 ዓ.ም አዲስ ዓመት መሸጋገሪያ አምስት የጳጉሜን ቀናትም በተለያዩ ዝግጅቶች ለማክበር ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።

በዚህም “ጳጉሜን-1 የመሻገር፣ ጳጉሜን-2 የሪፎርም፣ ጳጉሜን-3 የሉዓላዊነት፣ ጳጉሜን-4 የሕብር እና ጳጉሜን-5 የነገ ቀን” በሚሉ አምስት ስያሜዎች ይከበራል ብለዋል፡፡

ቀናቱ በሀገር ዓቀፍ ደረጃ በሁሉም ክልሎች፣ ከተማ አሥተዳደሮች፣ በመላው ዓለም በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ኮሚኒቲ አባላት እንደሚከበሩም ገልጸዋል፡፡

አምስቱ የጳጉሜን ቀናት ክብረ በዓልም የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመቋቋም በለውጡ መንግስት የተመዘገቡ ስኬቶችን ለማስቀጠል ዓላማ ያደረገ መሆኑን አብራርተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.