Fana: At a Speed of Life!

በስንዴ ምርታማነት የተገኘው ውጤት ኢትዮጵያን የማሻገር ምልክት መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በግብርናው መስክ በስንዴ ምርታማነት የተመዘገበው ስኬት ኢትዮጵያን የማሻገር ምልክት መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ ጳጉሜን 1 ቀን 2016 ዓ.ም የመሻገር ቀን “የመሻገር ጥሪቶች፤ የአዲስ ብርሃን ወረቶች” በሚል መሪ ሐሳብ እየተከበረ ይገኛል።

የኢትዮጵያን መሻገር ከሚያመላክቱ ነገሮች ውስጥ አንዱ ግብርና ነው፤ ከዚህም ውስጥ ስንዴ የአንበሳውን ድርሻ እየተወጣ ነው ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡

በኢትዮጵያ በተያዘው የመኸር ወቅት ብቻ ከ4 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ ሰብል የተሸፈነ ሲሆን÷ ከዚህም ውስጥ 70 በመቶው በኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴ መታረሱን ጠቅሰዋል፡፡

ይህም የኢትዮጵያ ግብርና ወደ ዘመናዊ እርሻ እየተሻገረ መሆኑን ያመላክታል ነው ያሉት፡፡

ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ስንዴ በዝናብ ወቅት ብቻ ሲመረት እንደነበር አስታውሰው÷ ከአምስት ዓመታት ወዲህ ግን በመስኖ በመዝራት ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን ለኢዜአ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት እራሷን ከመቻል አልፋ ባለፈው ዓመት ወደ ውጪ በመላክ ታሪክ ፈጽማለች ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ስንዴን በዓመት ሁለት ጊዜ በማምረት ሽግግር መመዝገቡንም ነው ያስረዱት፡፡

ከአምስት ዓመት በፊት በዝናብ የሚለማው ስንዴ 1 ነጥብ 75 ሚሊየን ሄከታር እንደነበር አስታውሰው÷ አሁን ከ 4 ሚሊየን ሄክታር በላይ መድረሱን አስታውቀዋል፡፡

ይህም ምርትና ምርታማነቱ ከእጥፍ በላይ በመጨመር በአንድ ሄክታር የሚገኘው 27 ኩንታል የነበረው ምርት አሁን በአማካይ 37 ኩንታል ደርሷል ነው ያሉት፡፡

ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴ፣ የኩታ ገጠም እርሻ፣ የተሟላ የግብዓት አቅርቦትና የካናይዝድ እርሻ በስንዴ ልማቱ ላይ በተሳካ ሁኔታ መተግበር መቻሉንም አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ግብርናን ከዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅ መንገድ ጀምራለች ያሉት ሚኒስትሩ÷ በአንዳንድ ቦታዎች በዓመት ሦስት ጊዜ የማምረት አቅም መፈጠሩን ገልጸዋል።

አርሶ አደሩ አሁን ላይ ከራሱ አልፎ የግብርናውን ሽግግር ለማሳለጥ ለወጪ፣ ለተኪና ለኢንዱስትሪ የሚሆኑ ምርቶችን በስፋት እያመረተ ነው ብለዋል፡፡

በሀገሪቱ 20 በመቶ የሚጠጋው የእርሻ ስራ በሜካናይዜሽን እየታረሰ መሆኑን ገልጸው÷ በቀጣይ ግብርናውን ከበሬ ትከሻ ለማላቀቅ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

ባለፈው ዓመት 8 ነጥብ 6 ሚሊየን ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም ዘዴ መታረሱን ጠቅሰው÷ በ2016/17 ምርት ዘመን ምጣኔውን ወደ 12 ነጥብ 4 ሚሊየን ሄክታር ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።

ስንዴ ላይ የተገኘውን ውጤት ወደ ሌሎች ምርቶች የማስፋት ሥራ እንደሚቀጥልም አመላክተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.