ሠላም በማጽናት የህብረተሰቡን መሠረታዊ ጥያቄዎች ለመመለስ በሙሉ አቅም ይሰራል – አቶ አሻድሊ ሀሰን
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2017 በጀት ዓመት ሠላምን በማጽናት የህብረተሰቡን መሠረታዊ ጥያቄዎች ለመመለስ በሙሉ አቅም እንደሚሠራ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ገለጹ።
ርዕሰ መሥተዳድሩ ለ2017 አዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት፤ የተጠናቀቀው ዓመት የተለያዩ ጫናዎችን በመቋቋም በሀገራችን የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ወደፊት የሚያራምዱ ስኬቶች ተመዝግበዋል ብለዋል፡፡
በክልሉ የነበረው የጸጥታ ችግር ተፈትቶ ሕዝቡ አንጻራዊ ሠላም ያገኘበት ዓመት እንደነበር አስታውሰው፤ የተገኘውን ሠላም በመጠቀምም መንግስት ህብረተሰቡንና ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ያከናወናቸው ተግባራት ውጤታማ እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡
በ2016 በጀት ዓመት በአሶሳ፣ ካማሺ፣ መተከል ዞኖችና በማኦና ኮሞ ልዩ ወረዳ በመንቀሳቀስ ከህዝቡ ጋር በሠላም፣ በልማትና በመልካም አስተዳድር ዘርፎች የተደረጉት ውይይቶች ትልቅ መነሳሳትን መፍጠራቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ከምንም በላይ ደግሞ በጸጥታ ችግሮቹ ሳይጠናቀቁ የቆዩ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት መደረጋቸው ትልቅ ስኬት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ክልሉ ካለው ዘርፈ-ብዙ አቅም ሕዝብ ተጠቃሚ እንዲሆን በመስዋዕትነት የተገኘውን ሠላም በአግባቡ መጠበቅ ይገባል ብለዋል፡፡
በ2017 በጀት ዓመትም የክልሉን ሠላም በማጽናት የህብረተሰቡን መሠረታዊ ጥያቄዎች ለመመለስ በሙሉ አቅም እንደሚሠራ አቶ አሻድሊ በመግለጫቸው ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን የጥንካሬያቸው መሰረት የሆነውን አብሮነት የበለጠ በማጠናከር ለትውልድ የምትመች ሀገር የመገንባት ሂደትን ዕውን እንደሚያደርጉም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የትናንት ድክመቶቻችን በማረም በተስፋ እና አቅሞቻችን ላይ የምንሠራበትን ጊዜና ጥራት በማሻሻል የብልጽግና ጉዟችንን ዕውን ማድረግ ይጠበቅብናል ያሉት አቶ አሻድሊ፤ ለዚህም ሕዝብ የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አዲሱን ዓመት ስናከብር የተቸገሩትን በመርዳት፣ መተሳሰባችንን የበለጠ በማሳደግ እና አብሮነታችንን በማጠናከር ሊሆን ይገባል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል።
አቶ አሻድሊ ሀሰን የ2017 አዲሱ ዓመት የሠላም፣ የፍቅር፣ የደስታ እና የብልጽግና ዘመን አንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡