የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ውሃ ተበክሏል በሚል የሚወራው ወሬ መሰረተ ቢስ መሆኑን አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ውሃ ተበክሏል በሚል የሚወራው ወሬ መሰረተ ቢስ መሆኑን አስታወቀ።
ባለስልጣኑ በሰጠው መግለጫ ዛሬ ከማለዳ ጀምሮ በአምስት የውሃ ማጣሪያ ማዕከላት ባደረገው የላቦራቶሪ ምርመራ ሁሉም የዓለም ጤና ድርጅት ባስቀመጠው መስፈርት መሰረት ደህንነታቸው የተጠበቁ መሆናቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል።
በላቦራቶሪ በተደረገው ምርመራ የክሎሪን መጠናቸው ያልቀነሰ መሆኑና የፒ ኤች መጠናቸውም ከሰባት እንዳልወረደ ባለስልጣኑ ማረጋገጡን ገልጿል።
የባልስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ዘሪሁን አባተ ሰሞኑን ከተፈጠረው አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ በመዲናዋ የተናፈሰው ወሬ ከእውነታው ጋር ፈፅሞ የማይገናኝ ነው ብለዋል።
ህብረተሰቡም አሁን እየደረሰው ያለው ንፁህ የመጠጥ ውሃ በዓለም አቀፍ መስፈርት መሰረት ጥራቱ የተጠበቀ በመሆኑ በተለመደው መልኩ እንዲገለገልም ባለስልጣኑ አሳስቧል።
በጸጋዬ ንጉስ