የኦሮሚያ ክልል ከሰሞኑ በተፈጠረው አለመረጋጋት የተፈናቀሉ ዜጎችን የማቋቋም ስራ እያከናወነ ነው
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኦሮሚያ ክልል ከሰሞኑ በተፈጠረው አለመረጋጋት ምክንያት ከቤት ንብረት የተፈናቀሉ ዜጎችን የማቋቋም ስራ እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ።
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ የነበራቸው የክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ የክልሉን ሰላምና መረጋጋት በማስጠበቅ አሁን የመንግስት ትኩረት የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደቀድሞ ህይወታቸው ለመመለስ መስራት ነው ብለዋል።
የጉዳቱን መጠን እና አይነት በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ቅኝት በማድረግ የንብረት ውድመት የደረሰባቸው፣ የተዘረፈባቸው እና የጠፋውን የሰው ህይወት ግንዛቤ ያስገባ ማጣራት የክልሉ መንግስት እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
በተለይም በቅድሚያ የክልሉን ሰላምና መረጋጋት የማስጠበቅ ስራ እየተሰራ ይገኛል ነው ያሉት።
ባለፉት ቀናት በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በታየው መረጋጋት የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ወደ ቀድሞ ህይወታቸው የመመለስ እና የማቋቋም የድጋፍ ስራው መቀጠሉንም አንስተዋል።
በየአካባቢው ህብረተሰቡ እያደረገ ያለው የበጎ ፈቃድ የድጋፍ የማሰባሰብ ተግባርም የሚደነቅ መሆኑንም አስረድተዋል።
የደረሰውን ጉዳትና መጠን በተመለከተም በዝርዝር በቀጣይ ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግም ገልጸዋል።
በሀይለየሱስ መኮንን