Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ 23ኛውን የአፍሪካ ቀንድ ኢንሼቲቭ የሚኒስትሮች ስብሰባ ታስተናግዳለች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) 23ኛው የአፍሪካ ቀንድ ኢንሼቲቭ የሚኒስትሮች ስብሰባ በፈረንጆቹ 2025 የካቲት ወር ላይ በአዲስ አበባ ከተማ እንደሚካሄድ ተገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው በዋሽንግተን ዲሲ ከተካሄደው የዓለም ባንክ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) ዓመታዊ ስብስባ ጎን ለጎን÷ በተደረገው 22ኛው የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሺዬቲቭ የሚኒስትሮች ስብስባ ላይ ነው፡፡

በስብሰባው ላይ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴን ጨምሮ የአፍሪካ ቀንድ ተወካዮች የተሳተፉ ሲሆን÷ ውይይቱ ጠንካራ የፋይናንስ ሁኔታን በመፍጠር የቀጣናውን ዘላቂ ዕድገት ማረጋገጥ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው፡፡

አቶ አሕመድ በዚሁ ወቅት የዓለም አቀፍ ትብብርን አስፈላጊነት ማስረዳታቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

በተጨማሪም ውይይቱ  በምሥራቅ አፍሪካ የወቅቱ አንገብጋቢ ጉዳይ የሆነው የአየር ንብረት ለውጥን ለመመከት የገንዘብ ድጋፍ ማግኘት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ማተኮሩ ተገልጿል፡፡

በአዲስ አበባ የሚካሄደው 23ኛው የሚኒስትሮች ስብሰባ ትኩረትም በቀጣናው ሀገራት መካከል የንግድ የትራንስፖርት እና መሰል የልማት ሥራዎችን በማጠናከር የኢኮኖሚ ውኅደት መፍጠር በሚቻልበት ሁኔታ እንደሚያተኩር ተጠቁሟል፡፡

የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ በፈረንጆቹ 2019 የተቋቋመ ሲሆን÷ ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ፣ ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን የኢኒሼቲቩ አባል ሀገራት ናቸው።

ኢኒሼቲቩ ሊያሳካቸው ላቀዳቸው ግቦችም እስከ አሁን 11 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር ሀብት መሰብሰቡ ተመላክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.