Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮ ቴሌኮምና የቱሪዝም ሚኒስቴር በጋራ ለመስራት ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮ ቴሌኮም እና የቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን በጋራ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለማዘመን ተስማምተዋል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ እና የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ የኢትዮ ቴሌኮምን የኮሙኒኬሽን እና የዲጂታል መሠረተ ልማት በመጠቀም የኢትዮጵያን ቱሪዝም ዘርፍ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በሚቻልበት ስትራቴጂ ላይ ተወያይተዋል፡፡

ውይይቱ በመከናወን ላይ ያለውን የቨርቹዋል ቱሪዝም ፕሮጀክት ከማጠናቀቅ በተጨማሪ በመላ ሀገሪቱ ቁልፍ በሆኑ የቱሪስት መዳረሻዎች ላይ ዘመኑ የደረሰበትን ኔትዎርክ በመጠቀም የጎብኚዎችን ተሞክሮ ለማሳደግ የታለሙ አዳዲስ ቴክኖሎጂ-ተኮር መፍትሄዎች ላይ ጠንካራ መሰረት ለመጣል ያተኮረ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

ውይይቱ የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ለማዘመን ከተለዩት ቁልፍ ስትራቴጂዎች መካከል እንደ “ኦግመንትድ ሪያሊቲ” እና “ቨርቹዋል ሪያሊቲ” ያሉ የላቁ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን ሥራ ላይ ለማዋልም የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡

የዲጂታል ቴክኖሎጂዎች ተግባራዊ መደረግ ጎብኚዎች የኢትዮጵያን እምቅ ባህላዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶች መስተጋብራዊ በሆነ መንገድ ለመረዳት እንደሚያስችልም ተገልጿል፡፡

ይህም ጎብኚዎች የቱሪዝም መዳረሻዎችን በአካል ተገኝተው የላቀ ተሞክሮ እንዲያገኙ ከማስቻል ባሻገር በቨርቹዋል ቱሪዝም የኢትዮጵያን የቱሪስት መዳረሻዎች ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው ከኢትዮ ቴሌኮም የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

በተጨማሪም ትብብሩ በዘመናዊ መተግበሪያዎች የቱሪዝም አገልግሎቶችን ለማዘመን የሚያስችል የጥሪ ማዕከል ማቋቋምንም ያካተተ ነው፡፡

ኢኒሼቲቮቹ አስፈላጊ መረጃዎችን በቀላሉ ለማግኘት፣ የክፍያ ሂደቶችን ለማቀላጠፍ እንዲሁም በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት ከጉብኝት እቅድ ጀምሮ እስከ ማጠናቀቂያ ድረስ ለማቅረብ ያስችላል ተብሏል፡፡

የስራ ሃላፊዎቹ የቱሪዝም ዘርፉን በዲጂታል የማዘመን ራዕይ እውን ለማድረግ እና ስትራቴጂካዊ ኢኒሼቲቮችን ለመተግበር የሚያስችል የፕሮጀክት ቡድኖች በማቋቋም ወደትግበራ ለመግባትም ከስምምነት ደርሰዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.