የተሃድሶ ስልጠና የወሰዱ የቀድሞ ታጣቂዎች ማኅበረሰቡን ተቀላቀሉ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 24፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል በሁለት ማዕከላት ትጥቅ በመፍታት የተሃድሶ ስልጠና የወሰዱ 640 የቀድሞ ታጣቂዎች ወደ ማኅበረሰቡ መቀላቀላቸውን የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን አስታወቀ።
ሰልጣኞቹ በመቐለና ዕዳጋ ሀሙስ ማዕከላት ስልጠናቸውን ተከታትለው ማጠናቀቃቸውን እና ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ መደረጉን በኮሚሽኑ የዲሞብላይዜሽን ዳይሬክተር ሌተናል ኮሎኔል ጎሳዬ ጥላሁን ተናግረዋል፡፡
በማዕከላቱ 1 ሺህ 360 የቀድሞ ታጣቂዎች የዲሞብላይዜሽን ሂደት ላይ እንደሚገኙ ገልጸው÷ በቀጣይ ወደ ማኅበረሰቡ እንደሚቀላቀሉ ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡
በዲሞብላይዜሽንና መልሶ ማቋቋም መርህ መነሻነትም ለሴቶችና አካል ጉዳተኞች ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የተሃድሶ ስልጠና መስጫ ማዕከላትን የቅበላ አቅም በማሳደግ በተቻለ ፍጥነት የቀድሞ ታጣቂዎች መደበኛ ሕይወታቸውን እንዲመሩ የማድረጉ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
በሚቀጥሉት አራት ወራት 75 ሺህ የትግራይ ክልል የቀድሞ ታጣቂዎች መደበኛ ሕይወታቸውን እንዲመሩ እንደሚደረገም አንስተዋል፡፡
በሁለት ዓመታት ውስጥም በሰባት ክልሎች በ1ኛ ዙር 75 ሺህ፣ በ2ኛ ዙር 100 ሺህ፣ በ3ኛው ዙር 150 ሺህ እንዲሁም በ4ኛው46 ሺህ፤ በድምሩ 371 ሺህ የቀድሞ ታጣቂዎችን የትጥቅ ማስፈታትና መልሶ የማቋቋም ሥራ እንደሚከናወን አመላክተዋል፡፡