Fana: At a Speed of Life!

በሕገ-ወጥ ነዳጅ ንግድ የተሠማሩ 34 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

 

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 24፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐዋሳ ከተማ በሕገ-ወጥ ነዳጅ ንግድ የተሠማሩ 34 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የሲዳማ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ ።

ሕገ-ወጥ የነዳጅ ግብይትን ለመቅረፍ ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ ወደ ሥራ መገባቱን እና ወደ ክልሉ የሚገባው ነዳጅ በፍትሐዊነት ለታለመለት ዓላማ እንዲውል እየተሠራ መሆኑን የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ሽመልስ ቶማስ አስታውቀዋል፡፡

በሐዋሳ በሕገ-ወጥ መንገድ ነዳጅ በፕላስቲክ ጠርሙስ እና በጀሪካን ይዘው ለመሸጥ የሞከሩ 32 ግለሰቦች እንዲሁም ማደያ ከተዘጋ በኋላ በምሽት ከማደያ ባለቤቶች ጋር በመመሳጠር ሲሸጡ የነበሩ እና ሲተባበሩ የነበሩ ሁለት የንግድና ኢንዱስትሪ ሠራተኞች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም የንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ መመሪያን ያላከበረ አንድ ማደያ በገንዘብ ሲቀጣ፤ ሌላ ማደያ አገልግሎት እንዳይሰጥ መታገዱን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አረጋግጠዋል፡፡

የነዳጅ ጉዳይ የመልካም አሥተዳደር ችግር እንደሚያመጣ በመገንዘብ ግብረ-ኃይሉ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ጥብቅ ቁጥጥር እያደረገ እና ሕጋዊ ርምጃ እየወሰደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በጸጥታ ኃይሉ የሚደረገው ክትትል እንደተጠበቀ ሆኖ ሕብረተሰቡ በሕገ-ወጥ መንገድ የነዳጅ ግብይት ሲፈጸም ካየ ወይም ከሰማ ለሲዳማ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በ8295 ወይም ለሐዋሳ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን በ1476 ነጻ የስልክ መስመሮች ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመሳፍንት እያዩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.