Fana: At a Speed of Life!

የገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑ ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 24፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝ ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

5ኛው ምዕራፍ የገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም የ2016 በጀት ዓመት፣ የ2017 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም እና የፕሮግራሙ 6ኛው ምዕራፍ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ባለድርሻዎች በተገኙበት ውይይት ተካሂዷል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት÷ የገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ነው ብለዋል፡፡

ፕሮግራሙ በማኅበረሰብ ሥራዎች እና በቤተሰብ ኑሮ ማሻሻያ እያደረገ ያለውን አበርክቶ አንስተው ለዚህም ዕውቅና መስጠታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡

ፕሮግራሙ የለጋሽ ድርጅቶች ሰብሳቢ ፈርዲናንድ ቮን ወይህ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ በ5ኛው ምዕራፍ የተመዘገቡ አመርቂ ውጤቶችን አብራርተው የተጀመሩ ሥራዎች በ6ኛው ምዕራፍም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡

የ6ኛ ምዕራፍ የትኩረት አቅጣጫዎችን በተመለከተ ሠነድ ያቀረቡት የምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ቤት ኃላፊ ስንታየሁ ደምሴ÷ የማኅበረሰብ እና የቤተሰብ ኑሮ ማሻሻያ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመላክተዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት 80 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር የተመደበ ሲሆን÷ ከዚህ ውስጥ 56 በመቶ መንግሥት 44 በመቶው ደግሞ በአጋር አካላት የሚሸፈን መሆኑ ተገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.