Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ የመሬት ይዞታ ካርታን ጨምሮ የተለያዩ ሃሰተኛ ሰነዶችን ሲያዘጋጅ የነበረ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ በተሰራው ድንገተኛ ኦፕሬሽን የመሬት ይዞታ ካርታን ጨምሮ የተለያዩ ሀሰተኛ ሰነዶችን ሲያዘጋጅ የነበረ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ፡፡

የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማን ጨምሮ በመላው አዲስ አበባ የትምህርት ቤት አካባቢ አዋኪ ድርጊቶችን የሚፈፅሙ ተቋማት ላይ ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱ ተገልጿል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ወረዳ ለቡ በተሰራው ኦፕሬሽን የመሬት ይዞታ ካርታን ጨምሮ የተለያዩ ሀሰተኛ ሰነዶችን ለተለያዩ እኩይ አላማ የሚያዘጋጅ የነበረ ግለሰብ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉ ተጠቁሟል፡፡

ቤቱ ሲፈተሽ የተገኙ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ግለሰቡ የጽንፈኛው ቡድን አባልና በትጥቅ ትግል ጭምር ተሳታፊ እንደነበር ተገልጿል፡፡

ከፎርጅድ ሰነዱ በተጨማሪ የተለያዩ የጦር ድምፅ አልባ መሳሪያዎችም በግለሰቡ ቤት መገኘታቸውን የአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

በክ/ከተማው በተሰራው ኦፕሬሽን ሺሻና ጫት ቤት፣ ግሮሰሪና ፔንሲዮን፣ ማሳጅ ቤትን ጨምሮ የትምህርት ቤቶች ዙሪያ በሚገኙ አዋኪ ተቋማትና ተሽከርካሪዎች ላይ ከ97 በላይ አስተዳደራዊና ሕጋዊ እርምጃዎች መወሰዳቸው ተገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.