የቼክ ሪፐብሊክ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የቼክ ሪፐብሊክ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የፈጠረውን ምቹ ዕድል ተጠቅመው በኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ ቀረበ።
የኢትዮ-ቼክ ሪፐብሊክ የጋራ ቢዝነስን ፎረም ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀምሯል።
የቼክ ሪፐብሊክ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የሠራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ማሪያን ጁሬስካ በመድረኩ መክፈቻ ላይ በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ የለውጥ ሥራዎች ውጤት ማስመዝገባቸውን በአዲስ አበባ ባደረጉት ጉብኝት ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ የሁለቱን ሀገራት የኢኮኖሚ ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በመድረኩ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የተካሄደው ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ ሀገራት መካከል አንዷ እንድትሆን ማድረጉን ገልጸዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ምቹ የኢንቨስትመንት ዕድል መፍጠሩን በመግለጽ የቼክ ሪፐብሊክ ኩባንያዎች እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
ቼክ ሪፐብሊክ በግብርና ምርቶቾ ማቀነባበሪያ መሣሪያዎች ኢንዱስትሪ ከፍተኛ ልምድ እና አቅም ያላት እንደመሆኗ በዘርፉ ከኢትዮጵያ ጋር የምታደርገውን ትብብር እንደምታጠናክር ተገልጿል።
የኢትዮጵያ የግብርና ምርቶችን መዳረሻ ከሆኑ ሀገራት መካከል ቼክ ሪፐብሊክ አንዷ ስትሆን በቀጣይ የበለጠ የኢትዮጵያ ምርቶች እንዲገቡ ለማድረግ እንደሚሰራ መገለጹን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል።