Fana: At a Speed of Life!

ያለ ደረሰኝ ሲነግዱ በተገኙ 1 ሺህ 145 ነጋዴዎች ላይ ርምጃ ተወስዷል

 

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ)በአዲስ አበባ ያለ ደረሰኝ የሚካሄደውን ንግድ ለማስቀረት በሚደረገው ቁጥጥር 1 ሺህ 145 ነጋዴዎች ላይ ርምጃ መወሰዱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ ::

የቢሮው የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሰውነት አየለ ÷አዲስ አበባ ሰፊ የገቢ አቅም ያላት መሆኑን ተከትሎ መሰብሰብ የሚገባወን የገቢ አቅም አሟጦ ለመሰብሰብ የተለያዩ የገቢ መሰብሰቢያ አማራጮች መዘርጋታቸውን አብራርተዋል ፡፡

ይህም ወደ ታክስ መረብ ያልገቡ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ ባርና ሬስቶራንት፣ ስጋ ቤቶች፣ አከራይና ተከራዮችን ወደ ታክስ መረብ የማስገባት ስራ መከናወኑን አስታውቀዋል፡፡

በከተማው ያለደረሰኝ የሚካሄደውን ንግድ ለማስቀረትና ከተማ አስተዳደሩ ማግኘት የሚገባውን ገቢ ለመሰብሰብ በከተማ አሰተዳደሩ የሚመራ ግብር ሀይል ተቋቁሞ ቁጥጥር እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተለይ ከመስከረም ወር ጀምሮ ቢሮው በዋነኝነት ትላልቅ ነጋዴዎች ላይ አስመጪ፣ አከፋፋይና እንደዚሁም አምራቾች ላይ ትኩረት በማድረግ የደረሰኝ ቁጥጥር ሲያደርግ ነበር ብለዋል ፡፡

በዚህም ባለፈው ህዳር ወር ብቻ 1ሺህ 145 ነጋዴዎችና ድርጅቶች ያለደረሰኝ ሽያጭ ሲያካሄዱ ተገኝተው እርምጃ እንደተወሰደባቸው መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሁሉም ገቢ መሰብሰቢያ አማራጮች 230 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ እየሰራ መሆኑን አቶ ሰውነት ጠቅሰዋል ፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.