Fana: At a Speed of Life!

ብልፅግና ፓርቲ በኢትዮጵያ አካታች የፖለቲካ ስርዓትና አሰባሳቢ ትርክትን በመፍጠር መሰረት ጥሏል – አቶ እንዳሻው ጣሰው

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ብልፅግና ፓርቲ በኢትዮጵያ አካታች የፖለቲካ ስርዓትና አሰባሳቢ ትርክትን በመፍጠር ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ተግባራት ማከናወኑን የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው ተናገሩ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ለዘመናት እየተንከባለሉ የመጡ ስብራቶችን በመጠገን ገዥና አሰባሳቢ ትርክቶችን የመፍጠር ስራ በስፋት መከናወኑን አንስተዋል።

በተለይም በሀገረ መንግስት ግንባታና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲሁም የብሄር ብሄረሰቦችን አጠቃላይ ተሳትፎ ያማከለ የፖለቲካ ስርአት በመፍጠር ረገድ ሰፊ ክፍተት እንደነበር አስታውሰዋል።

በመሆኑም በለውጡ ዓመታት አካታችና አሳታፊ የፖለቲካ ተሳትፎ እንዲኖር በማድረግ የተከናወኑ ስራዎች ዘርፈ ብዙ ውጤቶች የተገኘባቸው መሆናቸውን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ ገዥና አሰባሳቢ ትርክቶችን በመገንባት አካታች የፖለቲካ ሥርዓት መዘርጋት መቻሉን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ በቀጣይ የተጠናከረ ስራ የሚጠይቅ መሆኑንም ተናግረዋል።

ባለፉት ግዜያት የተፈጠሩ ስህተቶች በይቅርታ እና በንግግር መፍትሄ የሚያገኙበት ዕድል መፈጠሩን ጠቅሰው ሕዝቡን ወደ ህብረ ብሔራዊ አንድነት የሚያመጣ ለጋራ ዓላማ መሥራት የሚያስችል አሰባሳቢ ትርክት መገንባት መቻሉንም አንስተዋል።

ኢትዮጵያን ለመገንባት፣ በልማት፣ በሰላምና በዴሞክራሲ ግንባታ ረገድ ወደ ፊት ለማስኬድ የሁሉም ጥረትና ርብርብ አስፈላጊ መሆኑንም አንስተዋል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሠላም፣በልማትና በዴሞክራሲ ግንባታ ዙሪያ አሰባሳቢ አጀንዳዎችን በመለየት፤ ህብረተሰቡን በማሳተፍ ስኬታማ እንቅስቃሴዎች መደረጋቸውንም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በዚህም የህብረተሰቡ የልማት ተሳትፎና ተጠቃሚነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እንዲመጣ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.