ሰው ተኮር ስራዎች የብልጽግና ፓርቲን ሀገርን የመለወጥ ህልም የገለጡ ናቸው – ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ የኮሪደርና የመልሶ ማልማት ሰው ተኮር ስራዎች የብልጽግና ፓርቲን ሀገርን የመለወጥ ህልም የገለጡ መሆናቸውን የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት በለውጡ ዓመታት በአዲስ አበባ ከተማ የተገነቡና በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኙ የኮሪደር ልማት፣ የመልሶ ግንባታና ሰው ተኮር የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።
በእንጦጦ፣ ፒያሳ፣ ካዛንቺስ፣ ገላን ጉራና የአቃቂ ቃሊቲ የተቀናጀ የልማት መንደር፣ ለነገዋ የሴቶች የተድሶና የክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል እንዲሁም ብርሀን የዐይነ ስውራን አዳሪ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ጨምሮ የወንዝ ዳርቻ፣ ኮሪደርና የመልሶ ማልማት ተግባራትን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ከጉብኝቱ በኋላ፣ የመዲናዋ የወንዞች ዳርቻ ልማት እና በእንጦጦ የኮንሶ ወጣቶች የሚያከናውኑትን ገጸ ምድርን የማስዋብ ስራ ጨምሮ አዲስ አበባን ውበት የሚያላብሱ ተግባራት በመሳለጥ ላይ እንደሚገኙ መመልከታቸውን ገልጸዋል።
በፒያሳ አካባቢም ከአንድነትና ወዳጅነት ፓርኮች ጋር ተሰናስለው የሚገነቡ የወንዝ ዳርና የመልሶ ግንባታ ስራዎች የአትሌቲክስ ውድድሮችን ጭምር ማናስተናገድ በሚያስችል መልኩ እየተፋጠኑ ነው ብለዋል።
የልማት ሥራዎቹ ከቱሪዝም ዘርፍ የሚገኘውን የገቢ አቅም ለማሳደግ ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖራቸው ጠቅሰው የቦሌ ክፍለ ከተማ የአረንጓዴ ልማት እና የካዛንችስ ተነሺዎች የሚኖሩበት የገላን ጉራ የተቀናጀ የልማት መንደርም ለዜጎች ኑሮ ምቹ ሁኔታን የመፍጠር ተምሳሌታዊ ማሳያ ናቸው ብለዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ሰው ተኮር ነው ሲባልም አቅመ ደካማና ተንከባካቢ ያጡ ዜጎችን የመንከባከብና ህፃናትን የማስተማር ተግባር በማከናወን አንዱ መገለጫ አድርጎ እየሰራ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
የአዲስ አበባ የኮሪደር፣ የመልሶ ማልማት እና ሰው ተኮር ተግባራት የብልጽግና ፓርቲን ኢትዮጵያን የመለወጥ ህልም የገለጡ መሆናቸውን አንስተዋል።
በመዲናዋ እየተከናወኑ የሚገኙ የሀገርን ዕድገት የሚያፋጥኑ የልማት ሥራዎችን በሁሉም ክልሎች የማስፋት ሥራ መጀመሩንም ገልጸዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ፥ በመዲናዋ የሚከናወኑ የኮሪደር፣ የወንዝ ዳር እና የመልሶ ማልማት የመሰረተ ልማት ግንባታ ስራዎች ከተማዋን የሚያስውቡና ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሆናቸውን ገለጸዋል።
የመንገድ፣ የአረንጓዴ ልማት፣ የውሃ፣ የኤሌክትሪክ፣ የመኖሪያ ቤት፣ የቴሌኮሙኒኬሽንና መሰል የመሰረተ ልማት ግንባታ ተግባራቱም ለቀጣዩ ትውልድ ምንዳ መሆናቸውን አንስተዋል።
በአጠቃላይ የብልጽግና ፓርቲ በመዲናዋ እያከናወነ የሚገኘው የመሰረተ ልማት ግንባታ አዲስ አበባን ጽዱ በማድረግ ለአፍሪካ ምሳሌ የሆነች ከተማ መፍጠር የሚያስችል መሆኑን ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል፥ በመዲናዋ እየተገነቡ የሚገኙ ዘመናዊ መሰረተ ልማት ግንባታዎች ከፍተኛ የሥራ ዕድል የፈጠሩና አዲስ አበባን በአዲስ ምዕራፍ የሚያስቀምጡ ናቸው ብለዋል።
አዲስ አበባን ውብ ገጽታ እያላበሱ የሚገኙ ግዙፍ ፕሮጀክቶችም የብልጽግና ፓርቲን ለሰው ልጆች ቅድሚያ የሰጠ እሳቤ ያነገበ ፓርቲ መሆኑን እንደሚያሳዩ ተናግረዋል።