ድርጅቱ በቀን ከ1 ሚለዮን በላይ ሰዎችን እያጓጓዘ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በየቀኑ በምልልስ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ የሆኑ ዜጎችን እያጓጓዘ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት አስታወቀ።
የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አካሉ አሰፋ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት÷ ከሌሊቱ 11፡00 ሰዓት እስከ ምሽቱ 4 ሰዓት ድረስ በ988 አውቶቡሶች መደበኛ አገልግሎት እየተሰጠ ነው።
ባለፈው ዓመት በቀን 600 ሺህ ህዝብ በምልልስ ሲስተናገድ እንደነበር አስታውሰው፤ በተያዘው ዓመት የምልልስ አቅምን በማሳደግ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ ማድረስ መቻሉን ጠቁመዋል።
የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት በ182 መስመሮች አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን አንስተው፤ ባለፉት 6 ወራትም በምልልስ ለ198 ሚሊየን ሰዎች አገልግሎት መሰጠቱን ተናግረዋል ።
ድርጅቱ የመዲናዋን 30 በመቶ የትራንስፖርት ድርሻ ይሸፍናል ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው የተማሪ እና ሌሎች አገልግሎቶችን ጨምሮ በ1 ሺህ 140 አውቶቡሶች ለከተማው ህዝብ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
ድርጅቱ ባለፉት 6 ወራት ውስጥ የዕቅዱን 90 በመቶ ማሳካቱን ጠቅሰው፤ አሰራሩን፣ ቴክኖሎጂውን እና አደረጃጀቱን በማዘመን ከነበሩበት ችግሮች በመውጣት የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
በመሳፍንት እያዩ