በአዲስ አበባ ታቦታት ከመንበረ ክብራቸው በመውጣት ወደ 66 ጊዜያዊ ማረፊያ ይወርዳሉ
አዲስ አበባ፣ ጥር 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ታቦታት ከመንበረ ክብራቸው በውጣት ወደ 66 ጊዜያዊ ማረፊያ እንደሚወርዱ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክርስቲያን የፕሮጀክቶች መምሪያ ኃላፊ መላከ ሕይዎት አባ ወልደኢየሱስ ሰይፉ ገለጹ።
በአዲስ አበባ የጥምቀት በዓል በድምቀት የሚከበርበት ጃን ሜዳን ጨምሮ ሌሎች ቦታዎችን የማሳመር ስራ መከናወኑን ኃላፊው ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል።
“ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ የወረደበትን በማሰብ የከተራ በዓል ይከበራል” ያሉት አባ ወልደ ኢየሱስ÷ 14 ታቦታት ወደ ጃን ሜዳ ወርደው እንደሚያድሩ አመልክተዋል።
በጃን ሜዳ የሚደረገው ክብረ በዓል በተዋበ መልኩ እንዲደረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አስተዋፅዖ ማድረጉን ገልጸው ድጋፍ ላደረጉ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።
ምዕመናን ወደ ጃን ሜዳ በሚመጡበት ወቅት ከፀጥታ አካላት እና አስተባባሪዎች ጋር በመተባበር በዓሉ በድምቀት እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጠይቀዋል።
በዮናስ ጌትነት