ብልጽግና ፓርቲ የተገኙ ስኬቶችን ለማስቀጠልና ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ በትኩረት ይሰራል- አለሙ ስሜ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥር 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ብልጽግና ፓርቲ ያስመዘገባቸውን ስኬቶች አጠናክሮ ለማስቀጠልና ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ በትኩረት እንደሚሰራ የብልጽግና ፓርቲ የፌዴራል ተቋማት አደረጃጀት ሰብሳቢና የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለጹ።
የብልጽግና ፓርቲ የፌዴራል ተቋማት አደረጃጀት 2ኛ መደበኛ ጉባዔ ቅድመ ጉባዔ ኮንፈረንስ “ከቃል እስከ ባሕል”በሚል መሪ ሃሳብ ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ የብልጽግና ፓርቲ የፌዴራል ተቋማት አደረጃጀት ሰብሳቢና የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) እና የብልጽግና ፓርቲ የፌዴራል ተቋማት አደረጃጀት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ሃላፊ እና የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌን (ዶ/ር) ጨምሮ ሌሎች ሚኒስትሮችና የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
አለሙ ስሜ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት ፥ ኮንፈረንሱ የተሳካ ጉባዔ ለማካሄድና ጠንካራ ፓርቲ የመገንባት ትልምን ለማሳካት ያለመ ነው።
በኮንፈረንሱ ጥንካሬዎችን ለማስቀጠልና ውስንነቶችን በማረም ጠንካራና ፓርቲ ሆኖ ለመውጣት ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።
ብልጽግና ፓርቲ ያስመዘገባቸውን ስኬቶች አጠናክሮ ለማስቀጠል እና ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ በትኩረት ይሰራልም ነው ያሉት።
ሕብረ ብሔራዊ አንድነት፣ ወንድማማችነት እና አካታችነት የብልጽግና ፓርቲ መገለጫዎች መሆናቸውን አውስተዋል።
ተስፋዬ በልጂጌ (ዶ/ር) በበኩላቸው ፥ ኮንፈረንሱ የአባላቱንና አመራሩን የሥራ ሂደት በማነቀቃት እንዲሁም አቅማቸውን በማሳደግ በፈተና ወቅት ጸንተው እንዲቆሙ እንደሚያስችል አንስተዋል።
በተለያዩ ዘርፎች የተጀመሩ ልማቶችን ለማስቀጠል፣ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን መሰረት የሚጥል መሆኑን አብራርተዋል፡፡
አመራሩና አባላቱ ቃሉን በማደስና ተነሳሽነቱን በማጎልበት ሕዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራትን ለማከናወን ከፍተኛ መነሳሳትን የፈጠረ መሆኑንም ነው ያስረዱት፡፡
ስኬቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠልና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ነቅሶ በማረም ለቀጣይ ሥራ የጋራ አረዳድ የተፈጠረበት መሆኑን አስገንዝበዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔ ከፊታችን ጥር 23 እስከ 25 ቀን 2017 ዓ/ም እንደሚካሄድ ተመላክቷል።
በመላኩ ገድፍ