የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አግልግሎት ለከተራ እና ጥምቀት በዓላት ያስተላለፈው የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት፡-
ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለጥምቀት በዓል በሰላም አደረሳችሁ።
ጥምቀት ኢትዮጵያ ለዓለም ያበረከተችው የአደባባይ የወል በዓል ነው። በዓሉ ከሃይማኖታዊ በዓልነት ባሻገር የሚታይ ለዓለም በማይዳሰስ ቅርስነት የተበረከተ ሀብታችን ነው፡፡ የበዓሉ መሠረት ሃይማኖታዊ ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን ደግሞ ሃይማኖታዊ መሠረቱን እንደያዘ ባህላዊ እሴት እንዲኖረዉ ጭምር አድርገውታል፡፡
በዓሉ በየዓመቱ ሲከበር ከክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ባሻገር መላው ሕዝብ የሚታደምበት የዐደባባይ የወል በዓል ተደርጓል፡፡ ኢትዮጵያ ለዓለም ሕዝብ ያበረከተችው የማይዳሰስ ቅርስ ኾኖ መመዝገቡም ለዚህ ማሳያ ነው፡፡
የጥምቀት በዓል ከሌሎች የሃይማኖታዊ በዓላት ለየት የሚያደርገዉ በሃይማኖት ተቋማት ቅጥረ ግቢ ወይም በቤት ውስጥ ብቻ የሚከወን አለመኾኑና ደስታን ለአጠቃላይ ማኅበረሰቡ ማጋራቱ ነው፡፡ በሃይማኖታዊ እና ባህላዊ አልባሳት ያጌጡ ምዕመናንና ታዳሚዎች በጋራ የሚያከብሩት ድንቅ በዓል ነው፡፡
በዓሉ ከሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዐት፣ መዝሙሮች እና ባህላዊ ጭፈራዎች ባሻገር የገና ጨዋታ እና የፈረስ ግልቢያ መሰል ኹነቶች የሚያደምቁት ነው፡፡ ይህንን ትውፊቱን የጠበቀ በዓል ጎብኝዎች ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለመታደም ዐቅደዉ ይመጣሉ፤ የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ፣ የሕዝቧን አብሮነት እና እንግዳ ተቀባይነት ተመልክተዉበትም ይመለሳሉ፡፡
በዚህ በዓል ላይ የወጣቶች ተሳትፎ እና ሚና በእጅጉ ልቆ ይታያል፡፡ ታቦታቱን ከከተራ እስከ ቃና ዘገሊላ ድረስ በዝማሬ እና ጭፈራ ያጅባሉ፤ የታቦታቱን መንገድ ይጠርጋሉ፤ ምንጣፎችን ያነጥፋሉ፤ ይሸከማሉ፤ በገና ጨዋታና ፈረስ ጉግስ ይሳፋሉ፡፡ ይህ ጠንካራ ማኅበራዊ እሴት እየዳበረ መጥቷል፡፡
የጥምቀትንም በዓል ስናከብር ጥንታዊ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ ትውፊቱን ጠብቀን፤ የሃይማኖት አባቶች፣ ምዕመናን፣ ወጣቶች እና መላዉ ሕዝባችን የነበረ ሚናችንን እየተወጣን ሊኾን ይገባል፡፡ በዓሉ ደስታን የምንጋራበት የዐደባባይ በዓል ነውና ደስታችንን እየተጋራን ልናከብረው ይገባል፡፡
ለመላዉ የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች እና ለበዓሉ ታዳሚዎች በሙሉ እንኳን ለከተራ፣ ለጥምቀት እና ቃና ዘገሊላ በዓላት በሰላም አደረሳችሁ!
የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት