አፋር ክልል የምርጥ ዘር ፍላጎቴን በራስ አቅም ለመሸፈን እየሠራሁ ነው አለ
አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አፋር ክልል ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ የምርጥ ዘር ፍላጎቱን ሙሉ በሙሉ በራስ አቅም ለመሸፈን የሚያስቸለውን ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ፡፡
የምርጥ ዘር ፍላጎትን በራስ አቅም ለመሸፈን በጥናት የተደገፈ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አብዱ ኡትባን ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡
በዚሁ መሠረት የተለያዩ የሰብል ዓይነቶች፣ አትክልትና ፍራፍሬ እና የእንስሳት መኖ መሥራች እና ዋና የዘር ብዜቶች ሥራ በ700 ሔክታር ላይ እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ከዚህ ውስጥ በ400 ሔክታር ላይ እየለማ ያለው የስንዴ ምርጥ ዘር መሆኑንም ነው ያመላከቱት፡፡
ዘንድሮን ጨምሮ ላለፉት ዓመታት ምርጥ ዘር ከሌሎች አካባቢዎች ያመጡ እንደነበር አስታውሰው÷ ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ ፍላጎታቸውን በአራስ አቅም ለመሸፈን የሚያስችል ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ነው ያስታወቁት፡፡
ለዚህም የኢንተርፕራይዙ ይዞታ ከሆነው 700 ሔክታር በተጨማሪ በቀጣይ ዓመት በግብርና ዘርፍ ከተሰማሩ ባለሃብቶች፣ በእርሻ ዘርፍ ከተሰማሩ ማኅበራት እና ከፊል አርብቶ አደሮች ጋር ውል (ኮንትራት አግሪመንት) በመፈጸም ቢያንስ ከ1 ሺህ 400 በላይ ሔክታር ላይ ምርጥ ዘር በስፋት ለማልማት አቅደናል ነው ያሉት፡፡
አሁን እየለማ ያለው ምርጥ ዘርም ከ45 ቀናት በኋላ መሠብሠብ እንደሚጀምር እና ከዚህም ቢያንስ በሔክታር 40 ኩንታል ምርት እንደሚጠብቁ ጠቁመዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው