Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል 2 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ለወጣቶች ሥራ ዕድል ፈጠራ ተሰራጨ

አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አጋማሽ ለወጣቶች ሥራ ዕድል ፈጠራ 3 ነጥብ 98 ቢሊየን ብር ለማሰራጨት ታቅዶ 2 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ማሰራጨት መቻሉን የክልሉ ሥራ ዕድል ፈጠራ እና ክህሎት ቢሮ አስታወቀ።

ይህም ወጣቶችን ባንኮችን ጨምሮ ከተለያዩ የፋይንስ ተቋማት ጋር በማስተሳሰር የተሰራጨ ገንዘብ መሆኑን የቢሮው የኮሙኒኬሽንና ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ቶሎሳ አጃማ ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል።

በክልሉ በስድስት ወራት ውስጥ 1 ሚሊየን 890 ሺህ የሥራ ዕድል ለወጣቶች የተፈጠረ መሆኑን ጠቁመዋል።

ወጣቶቹም በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ እና በአገልግሎት ዘርፍ ወደ ሥራ መሰማራታቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ ከዚህም 54 በመቶው የግብርናው ዘርፍ እንደሚሸፍን ተናግረዋል።

ወደ ስራ ለተሰማሩ ወጣቶችም የእርሻ መሬትን ጨምሮ 39 ሺህ ሄክታር የማምረቻና መሸጫ ቦታዎች መቅረቡን ገልጸው፤ ወጣቶቹ ውጤታማ እንዲሆኑ የክህሎት ማሳደጊያ ስልጠናዎችን እንዲያገኙ መደረጉን አስረድተዋል።

እስካሁን በተሰራው ሥራ ጥሩ አፈፃፀም የታየ ቢሆንም ዜጎችን ይበልጥ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ በስፋት መሥራት እንደሚገባ ከአፈፃፀሙ አንፃር መገምገማቸውን አመልክተዋል።’

በአድማሱ አራጋው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.