ከብልሹ አሠራር ጋር በተያያዘ በ73 ሠራተኞች ላይ ርምጃ ተወሰደ
አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሌብነትና ብልሹ አሠራርን ለመከላከል ባለፉት ሥድስት ወራት በተከናወነ ሥራ በ73 ሠራተኞች ላይ አሥተዳደራዊ ርምጃ መውሰዱን የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
አሥተዳደራዊ ርምጃ ከተወሰደባቸው መካከል 25 በከባድ እና 48 በቀላል ዲስፒሊን መቀጣታቸውን የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዮናስ ዓለማየሁ ዛሬ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
በተጨማሪም የ37 ሠራተኞች ጉዳይ በፍርድ ቤት ሂደት ላይ እንደሚገኝ ነው ያስታወቁት፡፡
ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ከተያዘው መካከል ዘጠኝ የወረዳ ፈጻሚዎች፣ 11 ባለጉዳዮች እና 17 የማዕከል ሠራተኞች መሆናቸውንም አብራርተዋል፡፡
በሌላ በኩል 195 ሺህ 402 የልደት፣ 15 ሺህ 747 የጋብቻ፣ 3 ሺህ 769 የፍቺ፣ 11 ሺህ 376 የሞት እና 97 የጉዲፈቻ የሲቪል ምዝገባ አገልግሎት መስጠታቸውን ተናግረዋል፡፡
ከመታወቂያ አገልግሎት ጋር በተያያዘ 340 ሺህ ነዋሪዎች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ መመዝገባቸውን እና 268 ሺህ 470 ወገኖች ደግሞ የነዋሪነት መታወቂያ መውሰዳቸውን አንስተዋል፡፡
በ106 ጤና ተቋማት ላይ የአንድ ማዕከል የልደት ምዝገባ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸው÷ በፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት በ11 ምድብ ችሎቶችም የተሟላ የፍቺና ጉዲፈቻ ምዝገባ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡
ሕጻናት እንደተወለዱ በ90 ቀናት ውስጥ የልደት ምስክር ወረቀት እንዲይዙ ወላጆች በወቅቱ ማስመዝገብ እንዳለባቸው እና ጋብቻ፣ ፍቺ፣ ሞት እና ጉዲፈቻ ሲከሰቱም ሕብረተሰቡ በ30 ቀናት እንዲያስመዘግብ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው