በትራፊክ አደጋ ልጆቿን ወደ ትምህርት ቤት ስትሸኝ የነበረች እናትን ጨምሮ የ3 ሰዎች ሕይዎት አለፈ
አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከአዲስ አበባ ወደ ደብረ ብርሃን ሲጓዝ የነበረ የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪ ጠባሴ አካባቢ ሲደርስ መንገድ ስቶ በመውጣቱ የሦስት እግረኞችን ሕይዎት ቀጠፈ፡፡
ዛሬ ጠዋት 1 ሠዓት ከ30 ላይ በደረሰው የትራፊክ አደጋ÷ ልጆቿን ወደ ትምህርት ቤት ስትሸኝ የነበረች እናትን ጨምሮ የሦስት ሰዎች ሕይዎት ማለፉን የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል።
ከሟቾች በተጨማሪም በአደጋው የ1 ዓመት ከ7 ወር ሕጻንን ጨምሮ በ9 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል ጉዳት መድረሱን የመምሪያው የትራፊክ መረጃ ክፍል ኃላፊ ኮማንደር ኪዳኔ በቀለ አስታውቀዋል፡፡
የአደጋው መንስኤ ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር መሆኑንም ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል፡፡
አደጋውን ያደረሰው አሽከርካሪ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተጣራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በአላዩ ገረመው