Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በቴሌኮም መሰረተ ልማት እመርታዊ ለውጥ እያስመዘገበች መሆኗ ተገለጸ

 

አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በቴሌኮም መሰረተ ልማት ተደራሽነት እመርታዊ ለውጥ እያስመዘገበች መሆኗን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ።

በአዲስ አበባ ለሦስት ቀናት የሚቆይ የኢንተርኔት ልማት ጉባዔ መክፈቻ መርሐ-ግብር እየተካሄደ ነው፡፡

ሚኒስትሩ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር ኢንተርኔት ለኢኮኖሚ ዕድገት፣ ለማኅበራዊ ትስስርና ልማት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ጠቁመው፥ ለቀጣናዊ ትብብርና ለፈጠራ ማደግም ምቹ ምኅዳር የሚፈጥር ነው ብለዋል።

ሆኖም በቀጣናው ካለው ፍላጎት አንጻር የኢንተርኔት ተደራሽነት አሁንም ተግዳሮት ሆኖ መቀጠሉን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በዲጂታል 2025 ስትራቴጂ መሰረት የዲጂታል ሽግግርን እውን የሚያደርጉ ተግባራትን እያከናወነች እንደምትገኝም ጠቁመዋል፡፡

የቴሌኮም መሰረተ ልማትን በከፍተኛ ሁኔታ እያስፋፋችና እያዘመነች መሆኑን ገልጸው የ4ጂ ኔትወርክ ተደራሽነት ሀገራዊ ሽፋን 34 ነጥብ 8 በመቶ መድረሱን አንስተዋል።

5ጂ ኔትወርክም በትላልቅ ከተሞች አገልግሎት መጀመሩንና ይህም የኢንተርኔት ተደራሽነትንና ተጠቃሚነትን ያሳድጋል ነው ያሉት።

ኢትዮ ቴሌኮም የጀመረው ቴሌ ብር ከ51 ሚሊየን በላይ ተጠቃሚዎችን በማፍራት አካታች የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት ትልቅ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያ የጀመረችው የዲጂታል ሽግግር ሁሉንም ዜጎች ተጠቃሚ የሚያደርግ ዘመናዊ አገልግሎትና አካታች ኢኮኖሚን ለመገንባትና በአፍሪካ የዲጂታል አብዮት መሪ እንድትሆን የሚያስችል ነው ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.